360 ብር ለአንድ ሕጻን

ህሊና ጸጋዬ የአዲስ አበባ ነዋሪ ስትሆን ባንክ ቤት ተቀጥራ ነው የምትሠራው። የምትኖረው ደግሞ ከቤተሰቦቿ ጋር እንደሆነ ትናገራለች። በሜሪጆይ ''ስፖንሰርሺፕ'' ፕሮግራም ላይ የምትሳተፍ ሲሆን በየወሩ 360 ብር ድጎማ በማድረግ አንዲት የአራት ዓመት ሕጻንና እናቷን ትረዳለች።

ከልጅነቴ ጀምሮ ማኅበረሰባዊ ግዴታዬን የመወጣት ፍላጎት ቢኖረኝም ትምህርቴን ጨርሼ ሥራ እስክይዝ ድረስ ምንም ማድረግ አልቻልኩም ነበር ትላለች።

''በአጋጣሚ አብሮኝ ሥራ የሚሠራ ጓደኛዬ በፕሮግራሙ እንደሚሳተፍ ነገረኝና ስልክ ተቀብዬ ሙሉ መረጃ ማግኘት ቻልኩ። አሁን ሌላው ቢቀር የአንዲት ሕጻን ሕይወት ላይ አስተዋጽኦ እያደረግኩ ነው።''

በመጀመሪያ አንድ ልጅ አምጥታ ለመርዳት ብታስብም ስለፕሮግራሙ ከሰማች በኋላ ግን ሐሳቧን ቀይራ ሕጻኗን ከወላጅ እናቷ ሳትነጥል ለመርዳት እንደወሰነች ትናገራለች።

በዓላትን ጠብቃም ይሁን በሌላ ጊዜ ሕጻኗንና ቤተሰቧን እንደምትጎበኝና በቤቱ ውስጥ ሌሎች ሕጻናትም ስላሉ የቻለችውን ያክል እርዳታ እንደምታደርግላቸው ነግራናለች።

''እንደውም አንዳንድ ጊዜ ወደ ቤታቸው ስሄድ ሕጻኗ እኔን መለየት ጀምራለች። ታጫውተኛለች፤ ልሄድ ስል አትሄጂም ብላ ታስቸግራለች፤ አንዳንዴም እስከ በር ድረስ ትሸኘኛለች።''

የሜሪጆይ ውጥን

በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 2005 ዓ.ም ሜሪጆይ 10ኛ የምሥረታ በዓሉን ሲያከብር ነበር ''ፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ'' የሚባል ፕሮግራም ያስተዋወቀው። በሥሩ ከያዛቸው ፕሮግራሞች መካከል ዋንኛው ደግሞ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ከችግረኛ ቤተሰብ ለተገኙ ሕጻናት በበጎ ፈቃድ እጃቸውን የሚዘረጉበት መርሐግብር ነው።

በዚህ ሂደት በጎ ፈቃደኞች የችግረኛ ልጆችን ወጪ በየወሩ ይጋራሉ። ይህም ''ስፖንሰርሺፕ'' በመባል ይታወቃል።

ፕሮግራሙ ከተዋወቀበት ጊዜ ጀምሮም ወላጆቻቸውን ያጡና ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ እስከ 2000 የሚደርሱ ሕጻናት ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን፤ ከ700 በላይ ድርጅቶችና ግለሰቦች ደግሞ ተሳታፊዎች ናቸው፤ በሜሪጆይ ከፍተኛ ፕሮግራም ኦፊሰር የሆኑት አቶ ወንድወሰን መሰለ እንደገለጹት።

አንድ ግለሰብም ሆነ ድርጅት ለአንድ ሕጻን ድጋፍ አደርጋለው ብሎ የስፖንሰርሺፕ ፕሮግራሙ አካል መሆን ከፈለገ በየወሩ 360 ብር ብቻ መክፈል በቂ ነው።

350 ብር ምን ምን ይሸፍናል?

350 ብር በጣም ትንሽ ሊመስል ይችላል የሚሉት አቶ ወንድወሰን ፕሮግራሙን ሲጀምርም ከዛ ባነሰ የነበረ ሲሆን መጀመሪያ 140 ብር በመቀጠል 280 ብር እና በመጨረሻም 360 ብር ሆኗል።

ወርሃዊ መዋጮው ይህን ያክል ያነሰበት ምክንያት በአገሪቱ ያለውን የኑሮ ውድነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው ይላሉ አቶ ወንደወሰን።

''360 ብሩም የተጠቃሚዎቹን ችግር በዘላቂነት እንደማይፈታ እናውቃለን፤ ነገር ግን ዋናው ትኩረታችን በሕጻናቱና በተረጂዎቻቸው መካከል ቅርርብ መፍጠርና እንዲተዋወቁ ማድረግ ነው።''

ከዚህ ምክንያት በተጨማሪ ወላጆቻቸውን አጥተው ከዘመድ ወይም ጎረቤት አልያም ከችግረኛ ወላጆቻቸው ጋር የሚኖሩት ሕጻናት ድጋፉ ከመጀመሩ በፊት ኑሯቸውን የሚመሩበት የራሳቸው የሆነ መንገድ ስላላቸው፤ ሙሉ በሙሉ የተረጂነት ስሜት ውስጥ እንዲገቡ አይፈለግም።

አብዛኛዎቹ ቤተሰቦችና ሕጻናት የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት የሚፍጨረጨሩና አርፈው የማይቀመጡ ሰዎች በመሆናቸው፤ ይህን የአልሞት ባይ ተጋዳይነት ስሜታቸውን አዳክመን እርዳታ ጠባቂ እንዳይሆኑ የምንቆጣጠርበትም መንገድ ነው ብለዋል አቶ ወንደወሰን።

ድጋፍ ሰጪዎቹ በየወሩ ከሚያደርጉት የ360 ብር ድጋፍ በተጨማሪ በዓላትን ምክንያት በማድረግና የተለያዩ አጋጣሚዎችን በመጠቀም አልባሳት መግዛትና የትምህርት መሣሪያዎችን በስጦታ መልክ መስጠት አይነት ድጋፎችን ያደርጉላቸዋል።

''እነዚህን ነገሮች ሁሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንጂ 360 ብር በቂ እንዳልሆነ በደንብ እናውቃለን።''

ህሊና በአቶ ወንድወሰን ሐሳብ ትስማማለች። እሷ እንደምትለው 360 ብር ለአንድ ሰው ቀላል ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ሕጻናቱ ሌላው ቢቀር የሚበሉት ምግብ በትክክል ማግኘት ከቻሉና የትምህርት ቤት ወጪያቸው ከተሸፈነ ቀሪውን እራሳቸውና ቤተሰባቸው ተፍጨርጭረው ይሞሉታል ባይ ናት።

ከዚህ በተጨማሪ የገንዘቡ አነስተኛ መሆን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በአቅሙ ብዙ ሕጻናትን በያሉበት እንዲረዳ ዕድል ለመፍጠርም አልሟል።

"ምናልባት የልጆቹን ሁሉንም ዓይነት ፍላጎት ለማሟላት በሚል ገንዘቡ ከፍ ቢል፤ ብዙ ሰዎች መርዳት እየፈለጉ ጀምሬ ከማቋርጠው እያሉ ሊተዉት ይችላል" ትላለች።

ገንዘቡ ትንሽ ነው ብለው የሚያስቡም ካሉ ተጨማሪ ልጆችን መርዳት የሚችሉበት ወይም ደግሞ ከወርሃዊ ድጋፉ በተጨማሪ ለልጆቹ ብዙ ነገር ማድረግና ቤተሰቡንም ከመደገፍ የሚከለክላቸው እንደሌለም ትናገራለች።

የግለሰብ 'ስፖንሰሮች' ቁጥር ለምን አነሰ?

የመርሐ ግብሩ አስተባባሪ እንደሚሉት ብዙውን ጊዜ 100 እና ከዛ በላይ ሕጻናት በየወሩ የሚረዱት ትልልቅ ድርጅቶች ናቸው። ፕሮግራሙ ሲጀመር ጀመሮ የነበሩ ስፖንሰሮች ከጊዜ ብዛት ድጋፋቸውን እያቆሙ መጥተዋል።

ከእነዚህ ድርጅቶች መካከል አንዱ ደግሞ ዋሪት ሙሉጥላ ኢንተርናሽናል ይገኝበታል።

የድርጅቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆኑት ወይዘሮ ትህትና ሙሉሸዋ እንደሚሉት በዚሁ ፕሮግራም ስር ላለፉት ሰባት ወራት አስር ችግረኛ ህጻናትን ከቤተሰባቸው ሳይርቁ እርዳታ እያደረገ እንደሆነ ይናገራሉ።

ሌሎች ድርጅቶችም በመሰል ተግባራት ቢሰማሩ ብዙ ተስፋ ያላቸውና ተተኪ ሕጻናትን በሌሉበት መርዳት ይቻላል በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

አቶ ወንድወሰን ለቁጥሩ ትንሽ መሆን ያነሱት ዋንኛ ምክንያት ግን ከሰው ኃይል እጥረትና አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ መድረስ አለመቻላቸውን ነው።

በተለይ ደግሞ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎችን እንዲሁም የመንግሥትና የግል ድርጅቶችን ለመድረስ ሰፊ የሆነ የሰው ኃይልና የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚጠይቅም አልደበቁም።

እነዚህና ሌሎች ምክንያቶች አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ እንዳንደርስ አድርጎን ነው እንጂ ብዙ መርዳት የሚፈልጉ ዜጎች እንዳሉ እናውቃለን በማለት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።