የአፄ ቴዎድሮስ ቁንዳላ ሊመለስ ነው

የአፄ ቴዎድሮስ ቁንዳላ ከ150 ዓመታት በኋላ ሊመለስ ነው።

በመቅደላ ጦርነት ወቅት ለእንግሊዞች እጅ አልሰጥም ብለው ራሳቸውን ያጠፉት የአፄ ቴዎድሮስን ቁንዳላ ከ150 ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሊመለስ መሆኑን በእንግሊዝ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገልጿል።

በእንግሊዝ ሀገር በሚገኘው የብሔራዊ ጦር ሙዝየም በይዞታው ሥር የቆየውን የአፄ ቴዎድሮስ (መይሳው ካሳ) ቁንዳላ ለመመለስ መስማማቱን የተገለፀ ሲሆን በመጪው ሐሙስም ከኤምባሲው ጋር ውይይት ሊያደርግ ቀጠሮ ተይዟል።

አፄ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ በ1868 ዓ. ም. ከእንግሊዝ አገር ከመጡ 32 ሺ ወታደሮች ጋር ተዋግተው ራሳቸውን ማጥፋታቸውን ተከትሎ በሀገሪቷ ላይ ከፍተኛ ዘረፋ እንደተፈፀመ የታሪክ መዛግብት ያወሳሉ።

ምንም እንኳን የእንግሊዝ ጦር አዛዦች አፄ ቴዎድሮስ ይዘዋቸው የነበሩ እስረኞችን ለማስፈታት ነው ቢሉም የንጉሡን ቁንዳላ ከመሸለት በተጨማሪ መስቀልና የጣት ቀለበታቸውን፤ ሸሚዛቸውንና ሽጉጣቸውን ዘርፈዋል።

ከዚህም በተጨማሪ መጻሕፍት፣ የተለያዩ ከወርቅ የተሠሩ ቅርሶችን፣ መንፈሳዊ ሥዕሎችን፣ ታቦታት፣ ታሪካዊና ባሕላዊ ቅርሶች ሳይቀሩ ተዘርፈዋል፤ ቅርሶች ተቃጥለዋል፤ መጻሕፍትንም ቀዳደዋል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የጀግና ተምሳሌት የኾኑት የአፄ ቴዎድሮስ ቁንዳላ ወደ ሀገራቸው መመለስ ከፍተኛ ደስታን እንደፈጠረም ኤምባሲው በመግለጫው አስታውቋል።

በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ተመስገን ገበየሁ "የአጼ ቴዎድሮስ ቁንዳላ ወደ ኢትዮጵያ ሊመለስ በመሆኑ ደስ ብሎኛል" ብለዋል። በርካታ የአጼ ቴዎድሮስ የግል ንብረቶች በመቅደላው መዘረፋቸውን ገልጸው፣ የንጉሡ ቁንዳላ ሊመለስ መኾኑን በጎ ጅማሮ ነው ብለዋል።

"ይህ ጅማሮ ነው። ብዙ መመለስ ያለባቸው ቅርሶች አሉ፤ ይመለሳሉ ብዬ አምናለሁ"

የአጼ ቴዎድሮስ ቁንዳላ መመለስ ጎብኚዎችን ስለሚስብ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንደሚኖረው መምህሩ ተናግረዋል።