ዶናልድ ትራምፕን ከሥልጣን ለማባረር ተስፋ የተጣለበት ሕግ

የፎቶው ባለመብት, EPA
አሜሪካ በመሪዋ እንዲህ ተወዛግባ አታውቅም። ሕዝቧ ሁለት ጫፍ ረግጧል፤ ፕሬዝዳንቱን አምርረው በሚጠሉና ራሳቸውን እስኪስቱ በሚደግፏቸው ዜጎች መሀል።
ብዙዎች የትራምፕን የመጀመርያ ሳምንታት አያያዝ በማየት ሰውየው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከነጩ ቤተ መንግሥት በቅሌት እንደሚባረሩ ተስፋ አድርገው ነበር። እነሆ ሁለት ዓመት ደፈኑ።
አሁን "25ኛው ማሻሻያ" ተብሎ የሚጠራው ሕግ የአሜሪካንን ፕሬዝዳንት ከሥልጣን ለማውረድ ለጊዜው ብቸኛውና ተስፋ ሰጪው መንገድ ኾኗል። ነገሩ ከወዲህ በአሜሪካ ሚዲያ መነጋገሪያ መሆኑ 'ይህ ነገር የትራምፕን መጨረሻ ይሆን እንዴ?' የሚል ጥያቄን አጭሯል።
ይህ ጉዳይ መነጋገሪያ የሆነው የቀድመው የኤፍ ቢ አይ ተጠባባቂ ኃላፊ አንድሩ ማካቤ ትናንት '60 ሚኒት' በተሰኘው የቲቪ መርሐግብር ላይ ተገኝተው ፕሬዝዳንቱን ለማንሳት ውጥኖች እንደነበሩ የሚጠቁም አስተያየት ከሰጡ ወዲህ ነው።
ሕጉ ተፈጻሚ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
ይህ ሕግ ለአሜሪካ ሴኔት ርዕሰብሔሩን ለማሰናበት ዕድል ይሰጣል። የፕሬዝዳንቱ ካቢኔ ከደገፈው ደግሞ ነገሩ ያለቀለት ጉዳይ ይሆናል። ሆኖም በምክትል ፕሬዝዳንቱ ይሁንታን ማግኘት ይኖርበታል።
ሕጉ ተፈጻሚ የሚሆንበት አግባብ በጥቅሉ ርዕሰብሔሩ ታላቋን አገር አሜሪካንን ለመምራት በአንዳች ምክንያት ብቁ አይደለም ተብሎ ሲታመን ነው። ይህ የጤና መታወክንም ያጠቃልላል። በተለይ የአእምሮ ጤናን።
'ሰውየው በእርግጥ ጤነኛ ናቸው?' ብለው የሚጠይቁ አልጠፉም። ትራምፕ አሜሪካንን ለመምራት የሚያስፈልገው የጤነኝነት ደረጃን አያሟሉም ብለው የሚያምኑ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ይህንን ሕግ ለመጠቀም የትራምፕ የገዛ ካቢኔያቸውና ምክትል ፕሬዝዳንቱ አንድ እጅግ ወሳኝ ደብዳቤ ላይ መፈረም ይኖርባቸዋል።
ደብዳቤው "...ርዕሰብሔሩ ሥልጣናቸውንና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ባለመቻላቸው..." የሚል ሐረግን ይይዛል። ይህ ማለት ተቀማጩ ርዕሰ ብሔር ያቺን አገር ለመምራት አካላዊም ሆነ ሥነልቦናዊ ዝግጁነት ይጎድለዋል ተብሎ ታምኗል ማለት ነው። ስለዚህ ነገሩ በአመዛኙ አገር የማዳን ተግባር ኾኖ ይታያል።
እዚህ ዳብዳቤ ላይ የሚፈለገው ቁጥር ያላቸው ሴናተሮችና የካቢኔ አባላት ፈረሙ ማለት ትራምፕ በነገታው ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ነጩን ቤተ መንግሥት መልቀቅ ይኖርባቸዋል።
ምርጫ እስኪደርስም ምክትል ፕሬዝዳንቱ የአገሪቱ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሆነው ይቀጥላሉ።
ትራምፕ ከመሰናበታቸው በፊት ግን ውሳኔውን በመቃወም አንድ ደብዳቤ መጻፍ እንዲችሉ ሕጉ ይፈቅዳል፤ 25ኛው ማሻሻያ።
የታችኛውና የላይኛው ምክር ቤት 2/3ኛው ታዲያ ይህንን ሕግ ደግፎ ድምጽ መስጠት ይኖርበታል። ይህ ብቻም ሳይሆን ምክትላቸው ማይክ ፔንስም መፈረም ይኖርባቸዋል። እርሳቸው ካልፈረሙበት ተፈጻሚ አይሆንም።
በአሁኑ እውነታ ይህ የመሆን ዕድሉ ጠባብ የሚሆነው ታዲያ ሰውየው ለርሳቸው በሚያደገድጉ ካቢኔ አባላት መከበባቸው ነው። ሁለተኛው ፈተና የላይኛው ምክር ቤት የተሞላው በሪፐብሊካን መሆኑ ነው።
በአሜሪካ ታሪክ አንድም ጊዜ ይህ '25ኛው ማሻሻያ' የሚባለው ሕግ ተግባራዊ ሆኖ አያውቅም።














