ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ታዋቂ ኢትዮጵያዊያን አርቲስቶች ለመዋብ ምን ያህል ይከፍላሉ?
ኢትዮጵያ ውስጥ ታዋቂ አርቲስቶችን በትልልቅ መድረኮች እና ፕሮግራሞች ከማየት ባለፈ፤ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አማካይነት የአኗኗር ዘይቤያቸዉን በተለይም አለባበሳቸዉንና መዋቢያ መንገዳቸዉን መመልከት ተለምዷል።
አርቲስቶች ወደ ፋሽን ኢንዱስትሪዉ እንዲያማትሩ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች መካከል የፊልም ሠሪዎች የሽልማት ፕሮግራሞች፣ ቃለ መጠይቆች፣ የአልበም ወይም የፊልም ምርቃቶችን እና የማህበራዊ ሚዲያ የፎቶ ስብስቦች ይጠቀሳሉ።
ድምጻዊት ፀደንያ ገብረማርቆስ ለአለባበስ እና አቀራረብ የሚሰጠውን ትኩረት ስትገልፅ፣ "ከማቀርበዉ ሙዚቃ ባሻገር ለመታየትም መዘጋጀት አለብኝ፤ ታዋቂ ስትሆኚ ደግሞ ሰዎች አንቺን ለማየት ይጓጓሉ፤ ዘንጠሽ እንድትወጪ ይጠብቃሉ" ትላለች።
ብዙዎቹ አርቲስቶች በትልልቅ ፕሮግራሞች ላይ ለልብሶቻቸዉ አይከፍሉም። ለምን? ቢከፍሉ ኖሮ ምን ያህል ገንዘብ ያወጡ ነበር?
"የፋሽን ዘርፉ ገና ታዳጊ ስለሆነ አርቲስቶችን የምንጠቀማቸዉ እንደ ማስተዋወቂያ ነዉ። እነሱ አንድን ልብስ ከለበሱት በኋላ ብዙ ሰዎች ልብሱን ያዛሉ" በማለት ዲዛይነር ዮርዳኖስ አበራ ትናገራለች።
ዲዛይነር ሊሊ (የዮሃንስ ሲስተርስ ዲዛይን መስራች) እንደምትናገረው፤ ለተለያዩ ፕሮግራሞች የሚዘጋጁ የሴት አርቲስቶች አልባሳት በትንሹ ከ20,000 ብር ጀምሮ ይቀርባሉ። ከፍ እያለ ሲመጣ ከ40,000 እስከ 60,000 ብርም ሊደርስ ይችላል።
የወንዶች አልባሳት ዋጋ ከሴቶች ጋር ሲወዳደር "ሰማይ እና መሬት" ነዉ በማለት አክላም ታስረዳለች። ብዙ ጊዜ ባይሆንም ለሠርግ የወንድ ልብስ ለወራት ዲዛይን ተደርጎ በጣም ቢበዛ ከ15,000 እስከ 18,000 ብር ያወጣል።
ዲዛይነር እንቁጣጣሽ ክብረት (የእንቁ ዲዛይን መስራች) "እኔ ዲዛይን ያደረኳቸውን ልብሶች አርቲስቶችን ማልበስ አንዱ ስኬታማ የሆነ የማስታቂያ መንገዴ ነው" ትላለች።
የፋሽን ዘርፉ ቅድሚያ የሚሰጠው ለሴቶች ነው በሚል ቅሬታ የሚያቀርቡ ወንዶች እንዳሉም ትገልጻለች።
የማርዜል ሜካፕ ባለቤት የማሪያምወርቅ አለማየሁ ስለ ፊት መዋቢያ ዋጋ ስትገልጽ፣ "ዛሬ ዛሬ የፊት መዋቢያ በፋሽን ዘርፉ መታወቅ ጀምሯል። ብዙዎቹ ታዋቂ ግለሰቦች ዝግጅት ሲኖራቸው ለመዋብ ይመጣሉ" ትላለች።
ብዙዎቹ አርቲስቶች ሲዋቡ ተፈጥሯዊ ዉበትን የሚያጎላ የፊት መዋቢያ እንደሚጠይቁ የምትናገረው የማርያምወርቅ "ብዙ ኢትዮጵያዊያን የተጋነነ የፊት መዋቢያ አይወዱም" በማለት ትገልፃለች።
ፊት ማስዋብ በሴቶች ዘንድ የተለመደ ሲሆን፤ ወንዶች አሁን አሁን ለሰርግ ፊታቸዉን መሰራት እየጀመሩ ነው። የፊት መዋብያ ከፀጉር፣ ከጥፍር እና ሌሎች መዋቢያዎች አንፃር ይወደዳል።
ቀላል የፊት መዋቢያ ከ5,000 ብር ጀምሮ የሚቀርብ ሲሆን፤ ዋጋው ተጠቃሚዎች እንደሚፈልጉበት ወቅት ይለያያል። ለምሳሌ በሰርግ ወቅት ሲሰራ ዋጋው ከፍ ይላል።
በሰርግ ጊዜ እንደሚጠየቀው የጥቅል አይነት ለሙሽራ የአንድ ጊዜ የፊት መዋቢያ ከ7,000 ብር ጀምሮ እስከ 15,000 ብር ድረስ ይከፈላል።
የማርያምወርቅ እንደምትለው ብዙዎች በሰርግ ወቅት ጥቅል አገልግሎት ይጠቀማሉ። ጥቅሉም ከሰርግ በፊት፣ በሰርግ ቀን እና መልስን ያጠቃልላል። የዚህ አይነት የመዋብያ አገልግሎት ከ25 ,000 ብር እስከ 30,000 ብር አካባቢ ያስከፍላል።
ብዙዎች ፊታቸውን ሲዋቡ ፀጉራቸውንም በዚያው ይሰራሉ። ሰው ሰራሽ ፀጉር (ሂውማን ሄር) እንደጥራቱ ከ 7,000 ብር እስከ 20,000 ብር ድረስ ይሸጣል። የሰው ሰራሽ ፀጉር ከሚመረትባቸው ሀገራት እውቅ የሆኑት ብራዚል እና ጣልያንን ትጠቅሳለች።
የማርያምወርቅ "የቆዳ መዋዋቢያ አጠቃቀም ኢትዮጵያ ዉስጥ እንደ ፋሽን ቢመጣ ደስ ይለኛል። ብዙ ሰው ተፈጥሯዊ የመሰለ የፊት መዋቢያ ይፈልጋል። እንክብካቤ ያልተለየው ቆዳ ላይ የፊት መዋቢያ ሲጨመር ተፈጥሯዊ ይመስላል" በማለት እያደገ ያለዉን የፊት መዋብያ መጠቀም ልምድ ከቆዳ እንክብካቤ ጋር ታያይዘዋለች።