"አቀደች፣ አለመች፣ አሳካች" በሚል መሪ ቃል ጀግኒት ኮንፈረንስ ተጀመረ

ጀግኒትን የመረቋት ሴት ሚንስትሮች

የፎቶው ባለመብት, JegnitEthiopia Twitter

የምስሉ መግለጫ, ጀግኒትን የመረቋት ሴት ሚንስትሮች

ትላንት ረፋድ ላይ አዲስ የተመረጡ ሴት ሚንስትሮች በተገኙበት ጀግኒት ሀገር አቀፍ ንቅናቄ በይፋ ተጀምሯለች።

"አቀደች፣ አለመች፣ አሳካች" በተሰኘ መሪ ቃል የተጠነሰሰችው ጀግኒት፤ ዘላቂነት ያላት ንቅናቄ ብትሆንም፤ በመነሻ ቀኗ የሰላም ኮንፈረንስ ተካሂዷል።

የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚንስትር ወ/ሮ ያለም ጸጋይ እንደሚሉት፤ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች አንቱታን ያተረፉ እንስቶች ተሞክሯቸውን የሚያካፍሉባቸው መድረኮች ይዘጋጃሉ። ከውጣ ውረዳቸው በርካታ ሴቶች እንደሚማሩም ተስፋ ያደርጋሉ።

በእርግጥ ጀግኒትነት፣ ከግብ መድረስ፣ ለሴቶች አዲስ ነገር አይደለም። ንቅናቄዋ የስኬት ታሪኮችን አጉልታ እንድታወጣ ተወጠነች እንጂ።

ወደኋላ መለስ ብለው፤ በጨቋኝ ማህበረሰብ ውስጥ ታግለው ከፍታ ላይ የደረሱ አያቶቻችንን እንዲሁም እናቶቻችንን በማጣቀስ፤ ፈተና ቢበዛም ድል የሴቶች መሆኑን ይናገራሉ።

የጀግኒትነት መንፈስ ከትውልድ ትውልድ ይሻገር ዘንድ ተስፋ ሰንቀው፤ "ሁላችንም ጀግኒት ነን፤ ከድሮውም የነበረውን ነገር አጉልተን ማውጣት ፈልገን ነው እንጂ " ይላሉ።

ማህበረሰቡ "ሴቶች ይህን አይችሉም" "ያ ይከብዳቸዋል" የሚል የተዛባ አመለካከት ለዓመታት አስተጋብቷል። ይህም በአንድ ጀንበር የሚለወጥ አይደለም።

"ለውጥ የሚመጣው በሂደት ነው" ይላሉ ሚንስትሯ። ለውጡን ለማፋጠን መሰል አይን ገላጭ ንቅናቄዎች አስፈላጊ እንደሆኑም ያምናሉ።

በንቅናቄዋ የሚሳተፉት ሴት ሚንስትሮችና የእኩልነት አቀንቃኞች ብቻ ሳይሆኑ መላው ማህበረሰብ ይሆናል። ስለዚህም ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አንስቶ የተምሳሌት ሴቶች ተሞክሮ የሚዘከርባቸው መድረኮች ይሰናዳሉ።

በዋነኛነት፤ መውደቅ መነሳት የስኬት መንግድ መሆኑን ለታዳጊ ሴቶች ማስገንዘብ ይሻሉ። ሴቶችን ማነሳሳት ቀዳሚ ግባቸው ይሁን እንጂ ንቅናቄው ወንዶችንም ያማከለ ነው።

"ወንዶችም አጋርነታቸውን እንዲገልጹ እንፈልጋለን፤ የሁሉም ማህበረሰብ ንቅናቄ ነው" ሲሉ ወ/ሮ ያለም ያስረግጣሉ።

አገሪቱ ባለችበት ነባራዊ ሁኔታ እዚህም እዚያም የብሔር ግጭቶች ሲቀሰቀሱ ይስተዋላል። የብዙዎች ህይወት እየቀጠፈ ባለው ግጭት ቀዳሚ ተጎጂዎች ደግሞ ሴቶችና ህጻናት ናቸው።

ይህን እውነታ ታሳቢ በማድረግም የጀግኒት የመጀመሪያ ምዕራፍ ንቅናቄ፤ የሴቶችን ተጋላጭነት መቀነስ ላይ አተኩሯለች። ሚንስትሯ በየማህበረሰቡ ያሉ በግንባር ቀደምነት ሴቶችን ያማከሉ ባህላዊ ግጭት አፈታቶች ጎልተው እንዲወጡ፣ እንዲተገበሩ ማድረግም ለችግሩ ጊዜያዊም ቢሆን መፍትሄ እንደሚሰጥ ያምናሉ።

ጀግኒት ሙያ እና እድሜ ሳትለይ "ጀግኒት ጀግኒትን ትቀርጻለች" በሚል የመማማሪያ መድረክ እንድትፈጥር ይሻሉ። በግብርና፣ በምህንድስና. . . በሁሉም ዘርፍ።

ንቅናቄዋ በባለስልጣኖች ወይም ተደማጭነት ባላቸው ሴቶች የምትገደብ ሳትሆን፤ መሬት ላይ ወርዳ በመደበኛው ማህበረሰብ የእለት ከእለት ህይወት ተጨባጭ ለውጥ የምታመጣ ስለመሆኗም ወ/ሮ ያለም ተናግረዋል።

ሚንስትሯ፤ ንቅናቄዋ ዘላቂ ለውጥ እንደምታመጣ "ሴቶች በህይወት ተሞክሯቸው ላይ ተመስርተው እንዴት ችግሮች እንደሚታለፉ በተግባር ስለሚያሳዩ ይሳካል" ሲሉ ያስረዳሉ።