ከፀሐይ ኃይል ለአፍሪካ ኤሌክትሪክ ለማመንጨት የሚጥሩ ወንድማማቾች

የፎቶው ባለመብት, APTECH AFRICA
በዓለማችን ከአምስት ሰዎች አንዱ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አያገኝም። ሁለት ቢሊየን የሚገመቱ ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይልን የሚያገኙት ከእንጨት፣ ከሰልና ከመሳሰሉት ነዉ።
በቂ የኤሌክትሪክ አቅርቦት አለመኖር የአየር ብክለት ምክንያት ሆኖዉ የሚነሱ ነገሮችን ሰዎች ኤሌክትሪክ ለማግኘት ከሚጠቀሙዋቸዉ አማራጮች የሚመነጩ እንደሆኑም ይታመናል።
ኤርትራዊያኑ ወንድማማቾች፤ መትከል ዘርአይና ኢንጅነር ግርማይ ዘርአይ የአፕቴክ አፍሪካ መስራቾች ናቸዉ።
በ2006 በኤርትራ የተመሰረተዉ አፕቴክ አፍሪካ ከፀሐይ በሚገኝ ኤሌክትሪክና በፀሐይ የሚሰሩ የውሃ ፓምፖች በመስራትና በማቅረብ የሚንቀሳቀስ ተቋም ነዉ።
ይህ ተቋም በ2012 በደቡብ ሱዳን የተለያዩ ፕሮጀክቶች በመስራት እዉቅና እያገኘ መምጣቱን የሚናገረዉ መትከል ዘርኣይ፤ 2015 ላይ በኡጋንዳ አዲስ ቅርንጫት እንደከፈተ ይገልጻል።
ይህ ከፀሐይ ብርሃን ኃይል በማመንጨት ሥራ ላይ የተሰማራው ተቋም በሩዋንዳ፣ በሴራሊዮን፣ በመካከለኛው የአፍሪካ ሪፐብሊክና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እንዲሁም ላይቤሪያ ቅርንጫፎቹን በማስፋት እየሰራ ይገኛል።
አፕቴክ አፍሪካ በአፍሪካ ቀንድ ትልቁ በፀሐይ ኃይል የሚንቀሳቀስ የውሃ መሳቢያ ፓምፕ የሰራ ተቋም ሲሆን፤ የፀሐይ ኃይልን በሚጠቀም 82 ኪሎ ዋት የሚያመነጭ ሞተር በደቡብ ሱዳን ተክሏል።
"ባለን መረጃ መሰረት ከ345 ሺህ በላይ ሕዝብ ውሃ ያገኛል። 109 ሺህ የሚጠጋ ህዝብ ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኝ አድርገናል። እስከ አሁን 2.6 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጭ መሳሪያ ተክለናል" ይላል መትከል ዘርኣይ።
አብዛኛው ፕሮጀክት በገጠር አካባቢዎች የሚሰራ መሆኑን የሚናገረው ይህ ባለሙያ የውሃ፣ የኤሌክትሪክና የመሰል አገልግሎቶች ችግር በእነዚህ አካባቢዎች መፍታት ችለናል ይላል።
ደቡብ ሱዳን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ማዕከላዊ አፍሪካን በመሰሉ ይህ ፕሮጀክት የሚንቀሳቀስባቸዉ ሃገራት፤ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የሚፈትናቸዉ በመሆኑ ለብዙ ባለሀብቶች የሚመች ሁኔታ የላቸዉም ይላል።

የፎቶው ባለመብት, APTECHAFRICA
"የመፍትሄዉ አካል መሆንን መርጠናል"
መትከል ዘርአይ ይህ ሥራ የተጀመረበትን ሁኔታ ሲገልጽ "ታላቅ ወንድሜ ኢንጅነር ግርማይ ለረጅም ዓመታት በዚሁ ዘርፍ ስለተማረና ስለሰራ ከፀሐይ የኤሌክትሪክ ኃይል የማቅረብ ሥራን ልንጀምር ችለናል። በተለይ ደግሞ ዓለምን እየፈተናት ያለው የሙቀት መጨመር ሥራውን በሰፊው ወደዚህ ፕሮጀክት እንድንገባ ምክንያት ሆኗል" ይላል።
"የመፍትሄው አካል በመሆን ህፃናት ንጹህ ውሃ ሲጠጡ፣ ኤሌክትሪክ አግኝተዉ ሲማሩ፣ ማየትና ስደተኞች በውሃ ችግር ከሚመጡ በሽታዎች ሲጠበቁ ማየት የሚፈጥረው ደስታ የተለየ ነዉ" ሲል ይገልጻል።
ይህን ፕሮጀክት በስፋት ለማከናወን ትልቁ ችግር ገንዘብ እንደሆነ እነመትከል ይናገራሉ። ነገር ግን አፕቴክ አፍሪካ በ2020 ወደ አስር የአፍሪካ አገራት ሥራውን ለማስፋፋት ዕቅድ አለው ።
"ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት የሚኖር 600 ሚሊዮን የሚደርስ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ያላገኘ ህዝብ አለ። እኛ እየሰራንበት ባለው ቀጠናም በድህነት ስር ሆኖ ሻማ የሚጠቀምው ህዝብ፤ ሻማ በሚገዛበት ዋጋ ትንሽ በፀሐይ ኃይል የሚያመነጭ መሳሪያ በመስራት መፍትሄ ማበጀት የረጅም ጊዜ እቅዳችን ነው" ይላል መትከል።
ከዚህ ባሻገርም በገጠር በእርሻ የሚተዳደረው ማህበረሰብ በቂ የውሃ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችሉ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን በማምረት ለግብርና እንዲጠቀሙ ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን አክሏል።












