በደቡብ ክልል ሦስት ከተሞች በተፈጠሩ ግጭቶች 15 ሰዎች መሞታቸው ተገለፀ

በደቡብ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግስት አስተዳደር ውስጥ በሚገኙት የወልቂጤ፣ሀዋሳ እና ወላይታ ሶዶ ከተሞች በተፈጠሩ ግጭቶች 15 ሰዎች መሞታቸውን የክልሉ መንግስት አስታውቋል።

የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ሃይሉ ለሀገር ውስጥ የዜና ተቋማት እንደተናገሩት በግጭቱ ከሰዎች ህይወት መጥፋት በተጨማሪ "ግምቱ ያልታወቀ ንብረት ወድሟል፤ ከ2500 በላይ ሰዎችም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል" ብለዋል።

ግጭትወልቂጤ

ሰኔ 6 / 2010 ዓ.ም በወልቂጤ ከተማ የተፈጠረው ግጭት መንስኤ በከተማው እየተካሄደ ካለው የስፖርት ውድድር ጋር በተገናኘ የጉራጌ እና የአጎራባች ቀቤና ብሄረሰብ አባላት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እንደሆነ በወቅቱ የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ መናገራቸው አይዘነጋም።

ለመረጋጋት የፀጥታ ሃይሎችን ጣልቃ ገብነት ባስፈለገው በዚህ ግጭት የሁለት ሰዎች ህይወት መጥፋቱን የክልሉ የኮሚዩኒዮኬሽን ጉዳይ ኃላፊ ተናግረዋል ።

ለዘመናት በመልካም መግባባት የቆዩት የጉራጌ እና የቀቤና ብሄር አባላት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወልቂጤ ከተማ ይገባኛል ጥያቄ ልባቸውን እያሻከረው ስለመሆኑ በጉራጌ ዞን የመስቃን ወረዳ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳይ ባልደረባ ሬድዋን መሀመድ በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሀዋሳ ከተማ ግጭት

ሰኔ 5/ 2010 ዓ.ም የሲዳማ ብሄር የዘመን መለወጫ በዓል በሀዋሳ ከተማ በሚከበርበት ዕለት በተነሳ ግጭት እና ቀጥለው በመጡ ሁለት ቀናት በተፈጠሩ ውጥረቶች 10ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን፣9ሰዎች ከባድ ፣80 ደግሞ ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው የክልሉ መንግስት የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታውቋል።

ከ50 በላይ ብሄረሰቦች የሚኖሩበት የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦቹ ክልል ለተለያዩ የብሄር እና ጎሳ ግጭቶች እንግዳ ባይሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሲዳማ እና ወላይታ ብሄሮች መካካል የተፈጠረ ቁርሾ የውጥረት ምንጭነቱ እንደጎላ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የወላይታ ሶዶ ከተማ ግጭት

በሀዋሳው ግጭት ማግስት ሰኔ 8 /2010 ዓ.ም "የወላይታ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ብሄር ተኮር የነፍስ ማጥፋት እና ንብረት ማውደም ይቁም" የሚል እና ሌሎች መፈክሮችን የያዙ ሰልፈኞች ወደ ጎዳና ወጥተዋል።

ሆኖም ሰላማዊው ሰልፍ ከቆይታ በኋላ ወደ ግጭት ተለውጧል ።

ማሪያም ሰፈር ከሚባለው ስፍራ የተነሱ ሰልፈኞች በመጀመሪያ 'ጥቅማችንን እያስጠበቀ አይደለም!' ያሏቸውን የዞን አስተዳዳሪ ለማጥቃት ወደ መኖሪያ ቤታቸው እንዳቀኑ ፣ በመንገዳቸው ላይ ያገኟቸውን የግብርና መምሪያ፣የገጠር ቴክኖሎጂ ተቋማትን ፣ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት እና የግል ተቋማት ላይ ጉዳት እንዳደረሱ የዐይን መስክሮች በምስል እና ቪዲዮ አስደግፈው ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በዚህ ግጭት 3 ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡ የክልሉ መንግስት አስታውቋል።

ዶ/ር አብይ እንደ አስታራቂ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከአጭር የሶማሊያ ቆይታቸው መልስ ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ግጭት በተፈጠረባቸው ስፍራዎች ለሚኖሩ ዜጎች የሰላም ጥሪ አቅርበዋል።

በቀጣይ ቀናትም ወደ ስፍራው በማምራት ከህብረሰቡ ጋር ውይይት ለማድረግ ስለማቀዳቸውም አስታውቀዋል።