እንግሊዛዊው በሙስሊሞች ላይ ጥቃትን የሚያነሳሳ ፅሁፍ በማሰራጨት ተከሰሰ

ሙስሊሞች ላይ ጥቃት እንዲፈፀም የሚጠይቀው ደብዳቤ

የፎቶው ባለመብት, TellMamaUK

የምስሉ መግለጫ, ይህ ሙስሊሞች ላይ ጥቃት እንዲፈፀም የሚጠይቀው ደብዳቤ በድረገፆች ላይ በሰፊው ተሰራጭቷል

የእንግሊዝ የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል እንዳስታወቀው ግለሰቡ በሙስሊሞች ላይ ግድያ እንዲፈፀም የሚጠይቅ ጽሑፍ በማሰራጨት ተከስሷል።

ግለሰቡ ማክሰኞ ዕለት በቁጥጥር የዋለ ሲሆን መኖሪያ ቤቱና የመስሪያ ቤቱም ተበርብሯል።

ይህ ጥቃትን የሚያነሳሳ ጽሑፍ በማን እንደተዘጋጀ የማይታወቅ ሲሆን በመላው እንግሊዝ ሙስሊሞች ላይ የተቀነባበረ ጥቃት እንዲፈፀም ግን ይጠይቃል።

የ35 አመቱ ዴቪድ ፓንሃም የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው በ14 የተለያዩ ክሶች የተከሰሰ ሲሆን ከክሶቹ ዝርዝር መካከል ቦምብ የሚመስል ነገር በማዘጋጀት እንዲሁም ሽብር የሚነዙ ፅሁፎችን በማሰራጨት የሚሉ ይገኝበታል።

ግለሰቡ አርብ እለትም ፍርድ ቤት የሚቀርብ ይሆናል።

ዴቪድ ፓርንሃም የሚኖርበት አካባቢ የሚገኘው የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል ፖሊስም እንዳስታወቀው ግለሰቡ የተከሰሰው"እየተካሄደ ካለ ጠብ አጫሪ ተግባር ላይ ከመሳተፍ ጋር በተያያዘ ምርመራ ነው"

ግለሰቡ እጅ የተገኙት ፅሁፎች በተለያዩ የእንግሊዝ ከተሞች ለሚኖሩ ማህበረሰቦች መድረሱ ተረጋግጧል።