ኢትዮጵያና ሩሲያ የኒውክሌር ማበልፀጊያ ፕሮግራም በጋራ ለማካሄድ ተስማሙ

የኢትዮጵያ እና የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ዛሬ በአዲስ አበባ ጋዜጣዊ መግለጫ በጋራ ሲሰጡ

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።

ሚኒስትሮቹ ከውይይታቸው በኋላም የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ሁለቱ ሃገራት የኒውክሌር ቴክኖሎጅ ማዕከል ግንባታ በኢትዮጵያ ውስጥ በጋራ ለማቋቋም መስማማታቸውን ገልፀዋል።

የኒውክሌር ማበልፀጊያ ፕሮግራሙ በሁለቱ ሃገራት መካከል ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ወዲያውኑ እንደሚጀመር ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ተናግረዋል።

ሁለቱ ሃገራት 120 ዓመታት የዘለቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው የተናገሩት ሚኒስትሩ የምጣኔ ሐብት፣ ኢንቨስትመንት፣ በአፍሪካ ቀንድ የሰላም ሁኔታ እና በሌሎች ሁለቱ ሃገራት በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ መስማማታቸውን ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ተናግረዋል።

የኒውክሌር ማበልፀጊያ ፕሮግራሙ ለሰላማዊ አገልግሎት መሆኑንም ገልፀዋል።

በተጨማሪም ከአዲስ አበባ ወደ ሞስኮ በየቀኑ የቀጥታ በረራ ለመጀመር ስምምነት ላይ መደረሱም በዚሁ መግለጫ ላይ ተነግሯል።