ከሚሊዮን ዓመታት በፊት የነበረ የአስፈሪ ግዙፍ ፍጥረት ቅሪት ተገኘ

ቅሪተ አካሉ የተገኘው አስፈሪ ግዙፍ ፍጥረት

የፎቶው ባለመብት, LEONARDO ORTIZ

የምስሉ መግለጫ, ቅሪተ አካሉ የተገኘው አስፈሪ ግዙፍ ፍጥረት

በአርጀንቲና የአውቶብስ መጠን ያለው ነው የተባለ ግዙፉ ተሳቢ እና በራሪ ፍጥረት ቅሪተ አካል መገኘቱ ተሰምቷል።

የዚህ አስፈሪ በራሪ አካል ክንፍ ከአንደኛው ጫፍ እስከ መጨረሻው ድረስ 9 ሜትር የሚረዝም ሲሆን፤ ሌሎቸ እንስሳትን እያደነ ይመገብ እንደነበር ተገልጿል።

ቅሪተ አካሉን ያገኙት ባለሙያዎች "የሞት ድራጎን" ሲሉ ገልጸውታል።

ቅሪተ አካሉን ያገኙ ተመራማሪዎች አስተባባሪ የሆኑት ሊዎናርዶ ኦርቲዝ ቁመቱን ከቀጭኔ ጋር የሚስተካከል እንደሆነ ገልጸው፣ የክንፉ ስፋት ደግሞ ልንገምተው ከምንችለው መጠን በላይ ነው ይላሉ።

ፍጥረቱ እጅግ የሚያስፈራ ገጽታ እንደነበረውም ተጠቁሟል።

በአርጀንቲና የአንደስ ተራራዎች አለት ስር 86 ሚሊዮን ዓመታት የቆየው ቅሪተ አካል፣ ዳይኖሰር በሚኖርበት ወቅት ይኖር እንደነበር ያሳያል ተብሏል።

ፕሮፌሰር ኦርትዝ የተባሉ የቅድመ ቅሪተ አካላትን አፈጣጠር የሚያጠኑ ተመራማሪ፣ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2012 በቁፋሮ ነበር ያገኙት።

ቅሪተ አካሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ተማራማሪ ፍጥረቱን ታንቶስድራኮን አማሩ በሚል የግሪክ ቃል የሰየሙት ሲሆን ሞት እና ድራገን የሚል ትርጓሜን ይይዛል።

ፍጥረቱ ወፎች ከመፈጠራቸው አስቀድሞ ክንፍ ካላቸው እንስሳት የመጀመሪያዎቹ እንደሆነ ይታመናል።

የፍጥረቱ አኗኗር ሁኔታ ላይ የተደረገው ጥናት በቂ ነው ማለት አይቻልም ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ የተለያዩ መጠን ያላቸው በጣምራ መገኘታቸው ግን የተረጋገጠ ነው ብለዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2017 ከ170 ሚሊዮን ዓመታት በፊት ይኖር እንደነበረ የሚገመት እና 2.5 ሜትር እንደሚረዝም የተነገረለት ፍጥረት ተግኝቶ ነበር።