በኢትዮጵያ የሲሚንቶ ዋጋን አላስቀምስ ያሉት አራት ማነቆዎች

የፎቶው ባለመብት, J. Countess
በኢትዮጵያ ውስጥ በሚካሄዱ በርካታ የግንባታ ሥራዎች አማካይነት እውን ከሚሆኑ ጠቃሚ ግንባታዎች በተጨማሪ ዘርፉ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች የሥር ዕድልን እንደፈጠረ ይነገራል።
ይሁን እንጂ ዋነኞቹ የግንባታ ግብዓቶች በሆኑት በሲሚንቶ እና በብረት ላይ የሚታየው የዋጋ ንረት፤ በአገሪቱ እየተከናወኑ ላሉ የግንባታ ሥራዎች ዋነኛ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል።
በአገሪቱ የሚገኙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች፤ በስርጭት ችግር፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ በደኅንነት እጦት እና በጥሬ ዕቃ አቅርቦት መስተጓጎል ምርታቸው እየተፈተነ ነው። እነዚህም ዋጋቸው በከፍተኛ ደረጃ እንዲንር ምክንያት ሆነዋል።
ይህም የአገሪቱን የግንባታ ዘርፍ ከፍኛ እየጎዳው እንደሆነ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎችና ተቋማት ይናገራሉ።
ስርጭት
በኢትዮጵያ የሲሚንቶ ዋጋ ጣራ እንዲነካ ከፍተኛ ድርሻውን ከሚይዙት ምክንያቶች መካከል አንዱ በስርጭት ሥርዓቱ ውስጥ ያለ እንከን ነው።
ምርቱ ያለቀለት ሲሚንቶ ከፋብሪካ ወጥቶ የመጨረሻው ተጠቃሚ ጋር እስኪደርስ ድረስ ብዙ ሰንሰለቶችን ያልፋል። ፍቃድ ያላቸው ወኪሎች የሲሚንቶ ምርት ከፋብሪካ ተረክበው ለጅምላ አካፋፋዮች ያስረክባሉ። ጅምላ አከፋፋዮች ደግሞ ለቸርቻሪዎች ያቀርባሉ።
የቢቢሲ ሪፖርተር በአዳማ ከተማ ተዘዋውሮ የሲሚንቶ ዋጋ ሁኔታን ተመልክቷል። በዚህም ባለፉት ጥቂት ወራት የሲሚንቶ ዋጋ ከነበረበት 500 ብር ገደማ ጨምሮ ከ1ሺህ ብር በላይ እየተሸጠ መሆኑን ተረድቷል።
የኦሮሚያ ክልል ከሲሚንቶ ሰርጭት ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ሲሚንቶ የማከፋፈሉን ሥራ ከወኪሎች እጅ በማውጣት ኃላፊነቱን በማኅበር ተደራጅተው ለሚገኙ ወጣቶች ለመስጠት ስለማቀዱ ገልጿል።
አቶ ደረጄ ብርሃኑ ሲሚንቶ አከፋፋይ ወይም ወኪል ናቸው። አቶ ደረጄ ሲሚንቶ ከፋብሪካ ተረክበው 'በተመጣጣኝ ዋጋ' ለጅምላ ሻጮች እንደሚያከፋፍሉ ይናገራሉ የሚናገሩት አቶ ደረጄ፤ ለሲሚንቶ ዋጋ መናር ችግሩ ያለው ወኪሎች ጋር አይደለም ይላሉ።
"ፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃ በማጣታቸው ዋጋ ጨምረዋል። እንጂ ወኪሎች አይደሉም የጨመሩት። . . .ሌላው ዋጋ እየጨመሩ ያሉት ባለ ሱቆች ናቸው (ቸርቻሪዎች)። ብዙ ፈላጊ ስላለ ባለ ሱቆች ናቸው ዋጋ ጨምረው እየሸጡ ያሉት" ይላሉ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሲሚንቶ ሸማቶች እንደሚሉት ከሆነ አከፋፋዮች (ወኪሎች) ከፋብሪካ የሚረከቡትን ሲሚንቶ ለነጋዴዎች ከመሸጥ ይልቅ አየር በአየር ለደላሎች የሚሸጡበት አጋጣሚ እንዳለ ያስረዳሉ።
"እንደዚህ አይነቱ ለደላሎች አየር በአየር የመሸጥ ሥራ የሚሰሩ ሊኖሩ ይችላሉ" የሚሉት አቶ ብርሃኑ ሁሉም ግን በዚህ ድርጊት ውስጥ አሉበት ማለት እንደማይቻል ይገልጻሉ።
ሲሚንቶ በችርቻሮ የሚሸጡበት ሱቅ ያላቸው አቶ ሙሴ እምሩ ደግሞ በሲሚንቶ ስርጭት ውስጥ ፈተና የሆኑት ደላሎች መሆናቸውን በማንሳት፣ "እኛ የምንረከበው ከደላሎች ነው" ይላሉ።
ሲሚንቶ የሚያስረክቧቸው ደላሎች ሲሚንቶውን ከሌሎች ደላሎች በመግዛት የሚሸጡበት ሱቅ ሳይኖራቸው የምርት ዝውውሩን በስልክ ብቻ የሚያከናውኑ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።
እንደ አቶ ሙሴ ገለጻ ከሆነ ወኪሎች የሲሚንቶ ምርት ከፋብሪካ ከተረከቡ በኋላ ሲሚቶው የመጨረሻው ተጠቃሚ ጋር ከመድረሱ በፊት በአካፋፋዮች እና ከአንድ በላይ በሆኑ ደላሎች በኩል ያልፋል።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝደንት እና የሲሚንቶ ችግርን ለመቅረፍ የተቋቋመው ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አወሉ አብዲ ከሲሚንቶ ስርጭት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመቅፍ የክልሉ መንግሥት ወኪሎችን ከንግድ ሰንሰለቱ ሙሉ በሙሉ አስወጥቶ ስርጭቱ በተደራጁ ወጣቶች እንዲከናወን መወሰኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ወጣቶች አደራጅተን ማከማቻ እና የሽያጭ ቦታዎችን በየከተሞቹ እናዘጋጃለን። በፋይናንስ በኩልም ሁኔታዎች ይመቻቻሉ። ከሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎች ጋር አብረው እንዲሰሩ ይደረጋል" ብለዋል።

የባለሥልጣናት ቤተሰቦች በስርጭቱ ውስጥ መሳተፍ
ከሲሚንቶ ስርጭት ጋር ተያይዞ ከሚነሱት ወቀሳዎች መካከል የመንግሥት ባለሥልጣናት የቤተሰብ አባላትን ጨምሮ በጥቅም የተሳሰሩ የአከፋፋዮች ሰንሰለት አንዱ ሊሆን እንደሚችል በዘርፉ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ይናገራሉ።
በሲሚንቶ አከፋፋይነት ተሰማርተው ከሚገኙት መካከል ቢቢሲ ያናገራቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ግለሰቦች እንደሚሉት ይህ የተወሰኑ ባለሥልጣናት ቤተሰቦች እና ከእነሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች በስርጭቱ ውስጥ እንዳሉበት እንደሚወራ በመግለጽ በተጨባጭ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ አመልክተዋል።
ሌሎች ደግሞ በግላጭ ማንነታቸው ወጥቶ አይታወቅ እንጂ በተዘዋዋሪ ብዙም ባይሆኑ የተወሰኑ ግለሰቦች በስርጭቱ ውስጥ እጃቸውን እንዳስገቡ እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ከዚህ ቀደም የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ አባላት በሲሚንቶ ንግድ ውስጥ የባለሥልጣናት ቤተሰብ አባላት ተሳትፎ አላቸው በሚል እርስ በእርስ ሲካሰሱ እንደነበር ይታወሳል።
አቶ አወሉ አብዲ ግን በሲሚንቶ ንግድ ውስጥ የባለሥልጣናት የቤተሰብ አባላት ተሳታፊ ናቸው የሚባለውን እውነት አይደለም ይላሉ።
"የክልሉ ባለሥልጣናት የቤተሰብ አባላት በሲሚንቶ ንግድ ውስጥ ገብተዋል የሚላው በተደረገው ምርመራ ሐሰት መሆኑ ተደርሶበታል። ዘመድ ሳይሆን የዘመድ ዘመድ በሲሚንቶ ንግድ የተሳተፈ አልተገኘም" ይላሉ አቶ አወሉ።
"በአገር ደረጃ ዘጠና አካባቢ ወኪሎች ነው ያሉት። ከእነዚህ መካከል አንድም የባለሥልጣን ዘመድ የለም። በባለቤቶቻቸው ስም ሲሚንቶ እየነገዱ ነው የሚለው የሐሰት ወሬ ነው" ብለዋል።
የደኅንነት ችግር
በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሲሚንቶ የገበያ ድርሻውን ይዘው የሚገኙት በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ናቸው።
ዳንጎቴ፣ ደርባ፣ ሙገር፣ ኢትዮ ሴሜነን- በአንድ አካባቢ ይገኛሉ። በምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ። በእነዚህ ስፍራዎች ደግሞ እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው እና መንግሥት ሸኔ ብሎ አሸባሪ ሲል የፈረጀው ታጣቂ ቡድን ይንቀሳቀሳል።
ይህንን በታጣቂዎች የሚፈጠር የደኅንነት ስጋትን ለማስወገድ መንግሥት በግዙፍ ተቋማት አካባቢ ደኅንነትን ለማረጋገጥ የረዥም እና የአጭር ጊዜ እቅድ አውጥቶ እየሰራ እንደሆነ አቶ አወሉ ይናገራሉ።
"ወደፊት 'ኢንደስትሪያል ፎርስ' የተባለ ኃይል ተደራጅቶ ይህን የኢንዱስትሪ ደኅንነት እንዲያረጋግጥ አቅጣጫ ተቀምጧል። እስከዚያው ድረስ ደግሞ በቂ ፀጥታ ኃይል በአካባቢዎቹ እንዲሰማራ ከውሳኔ ተደርሷል" ይላሉ።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የውጭ አገር ዜጎችን ጨምሮ የሲሚንቶ ፋብሪካ ሠራተኞች በታጣቂዎች ታግተው ማስለቀቂያ ገንዘብ ተጠይቆባቸው ነበር። የአካባቢው ባለሥልጣናት ለዚህ እገታ ታጣቂውን ቡድን 'ሸኔ'ን ተጠያቂ አድርገው ነበር።
በቅርቡ ከሲሚንቶ ምርት እና ስርጭት ጋር ተያይዞ ላሉ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት ሽመልስ አብዲሳ፣ የማዕድን ሚንስትሩ ታከለ ኡማ እና ሲሚንቶ አምራቾች ውይይት አካሂደው ነበር።
በዚህ ውይይት ላይ የማዕድን ሚንስትሩ ከደኅንነት እጦት ጋር ተያይዞ ላሉ ቸግሮችን ለመፍታት የአካባቢው ወጣቶች በዘርፉ ላይ ያላቸውን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አንዱ መፍትሄ መሆኑን መግባባት ላይ እንደተደረሰበት ገልጸዋል።
ኢንጅነር ታከለ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ "የአካባቢው ወጣቶች በዘርፉ ላይ ያላቸውን ተጠቃሚነት ማስከበር በአንድ በኩል የወጣቶችን ህይወት የሚያሻሽል ሲሆን በሌላ በኩል ማኅበረሰበቡ በአካባቢው ለሚገኙ ተቋማት የሚኖሮውን የኔነት ስሜት የሚያሳድግ ነው። ይህም ለአካባቢው ሰላም እና ፋብሪካዎቹ የሚገጥማቸውን የፀጥታ ችግር ለማስቀረት የጎላ ሚና እንደሚኖረው ተግባብተናል" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, LEILAC
የውጭ ምንዛሬ እጥረት
ኢትዮጵያ ባለፉት በርካታ ዓመታት በተለይም የሰሜኑ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በውጭ ምንዛሬ እጥረት አዙሪት ውስጥ እንደምተገኝ የተለያዩ አስመጪዎችና ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
የውጭ ምንዛሬው እጥረት በኮንትራክሽን ዘረፉ ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይ ትልቁን ፈተና እንደደቀነ ከውጪ በሚመጡ ምርቶች ላይ የሚታየው የዋጋ መናር ቀላሉ ማሳያ ነው።
አምራቾች ከውጪ ለሚያስገቧቸው ግብዓቶቻቸው በውጭ ምንዛሬ መክፈል ይጠብቅባቸዋል። ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ደግሞ ለምርታቸው የሚያስፈልጓቸውን የድንጋይ ከሰል እና መለዋወጫዎችን ከውጭ ያስገባሉ።
አቶ አወሉም በኢትዮጵያ ከየሲሚንቶ ምርት ጋር ተያይዞ ያለው ዋነኛው ችግሩ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ነው ይላሉ።
በተደጋጋሚ እንደተጠቀሰው የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ለውጭ ምንዛሬ እጥረት ዘላቂው መፍትሄ አገሪቱ ለውጭ ገበያ የምታቀርበውን ምርት (ወጪ ንግድ) ላይ በርትቶ መስራት ሁነኛ አማራጭ ነው ይላሉ።













