ከጨረቃ በተወሰደ አፈር ለመጀመሪያ ጊዜ ተክሎችን ማብቀል ተቻለ

የፎቶው ባለመብት, UF/IFAS
ሳይንቲስቶች ከጨረቃ በተገኘ አፈር ተክሎችን ለመጀመሪያ ጊዜ ማብቀል ችለዋል።
ይህም ሁኔታ የሰው ልጅ በጨረቃ ረዘም ላለ ጊዜ መቆየት የሚያስችል መሆኑን ማሳወቅ የሚያስችል ወሳኝ እርምጃም ነው ተብሏል።
ተመራማሪዎች በአውሮፓውያኑ 1969 እስከ 1972 የአፖሎ ተልእኮዎች ወቅት የተሰበሰቡ ትናንሽ የአቧራ ናሙናዎችን ተጠቅመዋል።
በጣም የሚገርመው ሁኔታ ግን የዝሯቸው ዘሮች ከሁለት ቀናት በኋላ የመብቀል አዝማሚያ ማሳየታቸው ነው።
"ምን ያህል እንደተደነቅን ልነግራችሁ አልችልም" በማለት በግኝቶቹ ላይ የጥናት ጽሁፍ ያዘጋጁት የፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር አና-ሊዛ ፖል ተናግረዋል።
"እያንዳንዱ ተክል - ከጨረቃ በተገኘ አፈር ናሙናም ሆነ በመቆጣጠሪያ ውስጥ - እስከ ስድስት ቀን ገደማ ድረስ ተመሳሳይነት አለው" ብለዋል።
ከስድስት ቀናት በኋላ ግን ልዩነቶች መታየት ጀመሩ። በጨረቃ አፈር ውስጥ የበቀሉት ተክሎች በተወሰነ መልኩ መጫጨት ማሳየት ጀመሩ፤ ከሌሎች ጋር በንፅፅርም ቀስ ብለው ሲሆን ያደጉት መጨረሻም ላይ እድገታቸው አከተመ።
ነገር ግን የዚህ ምርምር ተሳታፊዎች በዋነኝነት የሚናገሩት ጉዳይ ከፍተኛ አንድምታ ያለው ግኝት ነው።
"ይህ ጥናት ለናሳ የረዥም ጊዜ ምርምር ወሳኝ የሚባል ነው። ጠፈርተኞች በጥልቅ ህዋ ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ በመቆየት ምርምር የሚያደርጉ ሲሆን በዚህም ቆይታቸው የምግብ አቅርቦት ስለሚያስፈልጋቸው በጨረቃ ላይ አትክልቶች መብቀል የመቻል ግኝት ጠቃሚ ነው" በማለት የናሳ ዋና አዛዥ ቢል ኔልሰን ተናግረዋል።
"ይህ መሠረታዊ የእጽዋት እድገት ጥናት ናሳ በምድር ላይ የምግብ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች አትክልቶች እንዴት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንዴት መቋቋም እንደሚችሉ የሚረዱን የግብርና ፈጠራዎችን የሚያነሳሳ ግኝት ነው" ብለዋል።
በግኝቱ ወቅት ለተመራማሪዎች አንዱ ፈታኝ ሁኔታ የነበረው ብዙ የጨረቃ አፈር ናሙና አለመኖሩ ነው።
ከአውሮፓውያኑ 1969 ጀምሮ ባሉት ሶስት አመታት ውስጥ የናሳ ጠፈርተኞች 382 ኪሎ ግራም የጨረቃ ቋጥኞች፣ ናሙናዎች፣ ጠጠሮች፣ አሸዋ እና አቧራ ከጨረቃ አምጥተዋል።
የፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ቡድን ለዚህ ሙከራ በተክል አንድ ግራም አፈር ብቻ ተሰጥቷል። እነዚህ ናሙናዎች ለበርካታ አሥርት ዓመታት ተቆልፈው የቆዩ ናቸው።.
ናሳ ከአውሮፓውያኑ 1972 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰዎችን በአውሮፓውያኑ 2025 በጨረቃ ላይ ለማሳረፍ አቅዷል።












