ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ የምታከብረው የድል በዓል ምን ያክል ትልቅ ነው?
በቭላድሚር ፑቲን አስተዳደር ይህ ቀን የአገሪቱን ወታደራዊ ጥንካሬና ያሏትን ከባድ የጦር መሳሪያዎች ለዓለም የምታሳይበት ሆኗል።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት 27 ሚሊየን የሶቪየት ሕብረት ዜጎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን ሩሲያውያንም ይህንን አጋጣሚ ታላቁ የአርበኝነት ጦርነት በማለት ይጠሩታል።
ሩሲያውያን ሞስኮ በሚገኘው ቀዩ አደባባይ እና ሌሎች ከተሞች በጎዳናዎች በመሰባሰብ ወታደራዊ ትዕይንቶችን በመታደም ያከብሩታል። ይህ ቀን 1945 ላይ ሩሲያ በናዚ ወታደሮች ላይ ድል የተቀዳጀችበትን ለመዘከር ያሰበ ነው። ይህ በዓል ዓመታዊ ትልቅ ትዕይንት እየሆነም መጥቷል።
የዘንድሮው በዓል ታድያ ለየት ባለ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚከበረው።
በናዚው ጦርነት አውሮጳን ነጻ ለማውጣት በሚል ነበር የሶቪየት ወታደሮች ጦርነት የዘመቱት። አሁን ላይ ግን ሩሲያ ለወራት ዩክሬን ላይ በኃይል ወረራ ፈጽማ ነው ይህንን የድል በአል የምታከብረው።
በዚህ ቀን በዩክሬኑ ጦርነት የተሳተፉና ትልቅ ሚና የነበራቸው በርካታ የሩሲያ ወታደሮች ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ፊት በመቆም ትዕይንት እንደሚያሳዩ የሚጠበቅ ሲሆን ፕሬዝዳንቱ ለዓለም ምን ዓይነት መልዕክት ያስተላልፉ ይሆን የሚለው የሚጠበቅ ጉዳይ ነው።
ይህ የድል ቀን የሶቪየት ሕብረት ሳትፈራርስ በፊት በትልቅ ድምቀት ይከበር የነበረ ሲሆን በአውሮጳውያኑ 1995 ላይ ፕሬዝደንት ቦሪስ ዬልሲን ለ50ኛ ዓመት እዮቤልዩ አከባበር በሚል እንደገና ማስከበር ጀምረው ነበር።
ነገር ግን ቭላድሚር ፑቲን ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በየዓመቱ እንዲከበርና ትልቅ ወታደራዊ ትዕይነት የሚደረግበት በአል እንዲሆን አድርገውታል።
የበርካታ ሩሲያውያን ማንነት እና ሩሲያ እንደ አገር ማንነቷ በራሱ በዚህ የድል በዓል ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ይነገራል።
አብዛኛዎቹ በሩሲያ የሚገኙ መማሪያ የታሪክ መጽሐፍት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አውሮጳን ከጨቋኙ የናዚ ስርዓት ነጻ ያወጣችው ሩሲያ እንደሆነች በስፋት ይገለጻሉ።
''ከጦርነቱ በፊት በነበሩት ዓመታት እንኳን ይህ በዓል የሩሲያ ኃያልነት እንዲሁም የፑቲን ቁጥጥርና የበላይነት የሚታይበት ቀን ነው'' ይላል በግላስኮ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ አሞን ቼስኪን።
በዚህ ቀን የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ላይ ያወጁትን ጦርነት ማብቃት ያበስራሉ የሚሉ ጭምጭምታዎች ቢኖሩም እውነት የመሆን እድላቸው ግን በጣም አነስተኛ ነው።
በሌላ በኩል እንደውም ሩሲያ ሙሉ ኃይሏን በመጠቀም በዩክሬን ላይ የምታካሄደውን ወረራ እንደሚያጠናክሩ የሚገልጹበት አጋጣሚም ይሆናል ተብሎ ነበር። ነገር ግን የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌ ላቭሮቭ መከላከያ ኃይሉ ቀን እየቆጠረ አካሄዱን እና አሰራሩን የሚቀያይር አይደለም ሲሉ ተደምጠዋል።
ሩሲያ በአውሮጳውያኑ 2014 ላይ ክሪሚያን ከዩክሬን ነጥቃ የራሷ ካደረገች በኋላ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዚህ በዓል ላይ በመገኘት ባደረጉት ንግግር ፋሺዝም ላይ ድል መቀዳጀታቸው ተናግረው ነበር።
''በዘንድሮው የድል በዓል ላይ የካቲት ወር ላይ መጠናቀቅ የነበረበት የዩክሬን ጦርነትን ድል ለማብሰር ነበር የታቀደው። ይህንን አስመልክቶ የሩሲያ መንግሥት የተለያዩ የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን አጠናቅቋል። ሩሲያውያን መንግሥታቸው ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ በማለት የጠራው ወረራ ምን ያክል አስፈላጊ ነበር፤ ውጤታማስ ነበር ወይ ብለው መጠየቅ አለባቸው'' ይላሉ በፖሊሽ ራሺያን ዲያሎግ የሚሰሩት አርነስት ዋይቺስኪዊዝ።
የዩክሬንን መንግሥት ከስልጣን ማስወገድ ተብሎ የተጀመረው ወታደራዊ እንቅስቃሴ የታሰበለትን ዓላማ ማሰካት ሳይችል ቀርቷል። በምትኩም ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሞሪዮፖል ከተማን አብዛኛውን ክፍል መቆጣጠር እንደ ትልቅ ድል ተደርጎ ለማየት ተገድደዋል።
''በአብዛኛዎቹ የሩሲያ ትላልቅ ከተሞች የድል በዓልን የተመለከቱ ምልክቶችና መልዕክቶችን እየተመለከትን ነው። ከዚህ በፊት ሜይ 9 1945 የሚል ጽሑፍ ነበር የሚለጠፈው፤ አሁን ላይ ግን 1945/ 2022 የሚል ተጨምሮበታል። ይህ ደግሞ ሩሲያውያን ዘንድሮም ጸረ ናዚ ውጊያ እያደረጉ እንደሆነ ለማሳመን የሚደረግ ነው'' ይላል ሩሲያዊው ኦልጋ ኢሪሶቫ።
ሌላው ቀርቶ ማሪዮፖል ውስጥ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት የድል በዓልን አስመልክቶ ምንም አይነት ትዕይንት አይኖርም። አካባቢውን እንዲያስተዳድሩ በሩሲያ መንግሥት የተሾሙት ዴኒስ ፑሺሊን በበኩላቸው በዓሉን ለማክበር የማሪዎፖል ግዛት የዶኔስክ ህዝቦች ሪፐብሊክ አካል እስከምትሆን እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
ነገር ግን እስካሁን ግልጽ ያልተደረጉ የተለያዩ አከባበሮች የሚኖሩ ሲሆን አብዛኛዎቹም ሩሲያ በምትቆጣጠራቸው አካባቢዎች ነው የሚሆነው። ከበአሉ ቀናት በፊትም ታዋቂው የሩሲያ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዳይሬክተር ቭላድሚር ሶሎቭዮቭ በከተማዋ እንደነበረና ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሰርጌ ኪርዬንኮ የተገኙበት ልኡካን ቡድን ተገኝቶ እንደነበር ተገልጿል።
ይህ በቀዩ አደባባይ የሚከበረው የድል በዓል ቀን ሩሲያ አሉኝ የምትላቸውን የተራቀቁ ወታደራዊ መሳሪያዎቿን የምታሳይበት ትልቅ አጋጣሚ ነው። 2015 ላይ ይህ በዓል በሚከበርበት ወቅት ሩሲያ ይፋ ያደረገችው ቲ-14 የተሰኘ ዘመናዊ መሳሪያ አስተዋውቃ ነበር። ነገር ግን አሁን ላይ በዩክሬኑ ጦርነት ይህ መሳሪያ ጥቅም ላይ አልዋለም። ምናልባት ሩሲያ ለውጊያ እንኳን ዝግጁ ያልሆኑ አዳዲስ መሳሪያዎችን በዚህ በዓል ላይ እንደምታሳይ ይገመታል።
በዘንድሮው በዓል ለትዕይንት የሚቀርቡት መሳሪያዎችም ሆነ የወታደሮች ቁጥር እንደሚቀንስ ይጠበቃል። ነገር ግን ከ10 ሺ ያላነሱ ወታደሮችና 129 ወታደራዊ መሳሪያዎች በበዓሉ አከባበር ላይ እንደሚገኙ ቢቢሲ ሩሲያ ያገኘው መረጃ ይጠቁማል።
የአየር ኃይሉ የሚያሳየው ትዕይንት ግን ከሌላ ጊዜው ያነሰ እንደማይሆን ይጠበቃል። 77 ወታደራዊ አውሮፕላኖች እና ሄሊኮፕተሮች በቀዩ አደባባይ አካባቢ ልምምድ ሲያደርጉ ከርመዋል። ነገር ግን በዘንድሮው በዓል ላይ ማንኛውም ዓይነት የውጭ አገር መሪ የማይታደም ሲሆን ከሌሎች ዓመታት አንጻር 77ኛው የድል በዓል ቀዝቃዛው እንደሚሆን ተገምቷል።
የዘንድሮውን የድል በማስመልከት የሚተላላፉት አብዛኛዎቹ መልዕክቶች የሩሲያ ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ናቸው። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የነበረውን የጸረ ናዚ አስተሳሰብ መልሶ ለማምጣትና ህዝቡ ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ለማድረግ እየተጣረ እንደሆነ ኦልጋ ኢሪሶቫ ያስረዳል። ምክንያቱም በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አብዛኛው ሩሲያዊ የሆነ የቤተሰብ አባሉን አጥቷል።
ምንም እንኳን ሩሲያ ዩክሬን ላይ ጦርነት ባወጀችበት ወቅት በዓሉን ለማክበር ደፋ ቀና ብትልም በዙሪያዋ ያሉ ጎረቤት አገራት ግን ብዙም ትኩረት የሰጡት አይመስልም። የዩክሬን አካባቢ ከናዚ ወታደሮች ጋር በተደረገው ጦርነት ከባድ ኪሳራ ማስተናገዱን ተከትሎ ዩክሬናውያን ከድል በዓልነት ይልቅ የሞቱትን የምናስብበት ነው ብለዋል።
ካዛኪስታን ደግሞ ለሦስተኛ ጊዜ ቀኑን በማስመልከት የምታደርገውን ወታደራዊ ትዕይነት ሰርዛለች። ጎረቤት ላትቪያ ደግሞ ቀኑን በዩክሬን ሩሲያ ጦርነት ለሞቱ ሰዎች መታሰቢያ ይሁን ብላለች።