ወድቆ ያገኘውን 50ሺህ ዶላር መልሶ ሕይወቱ የተቀየረው የታክሲ ሹፌር

ኢማኑኤል ትምህር ክፍል ውስጥ

የ19 ዓመቱ ወጣት ወድቆ ያገኘውን 50ሺህ የአሜሪካ ዶላር ለባለቤቱ ከመለሰ በኋላ የሕይወቱ አቅጣጫ ተቀይሯል።

ወጣቱ አቋርጦት ወደነበረው የትምህርት ገበታ ተመልሷል። ቢያንስ በስድስት ዓመት ከሚያንሱት ተማሪዎች ጋር የመማሪያ ክፍል እየተጋራ ነው።

ሞተር ሳይክል እየሸከረከረ የታክሲ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው የላይቤሪያው ወጣት አንድ ቀን የሕይወቱን አቅጣጫ የቀየረ ነገር አገኝ።

ኢማኑኤል ቱሎኢ በፌስታል የተጠቀለለ 50ሺህ ዶላር ከመንገድ ዳር ወድቆ አገኘ።

በድህነት ለሚኖረው ኢማኑኤል ይህ ትልቅ ገንዘብ ነው። ያገኘው ዶላር ኪሱ ቢገባ ሕይወቱን መቀየር የሚችል ገንበዝ ነው። ኢማኑኤል ግን ገንዘቡን ለባለቤቱ ለመመለስ ወሰነ።

ገንዘቡን የጣለው የአፋልጉኝ ማስታወቂያውን በራዲዮ ሲያስነግር ኢማኑኤል ዶላሩን ይዞ ወደፊት መጣ።

ኢማኑኤል በታማኝነቱ በብዙዎች ተተቸ። ሞኝ ተባለ። ብዙዎች ተሳለቁበት። በድህነት ኖረህ ድሃ ሆነህ ትሞታለህ አሉት። በኢማኑኤል ቅንነት የተደነቁም አልጠፉም። ሪክስ ኢንስቲትዩት የተባለ ቅንጡ አዳሪ ትምህርት ቤት በነጻ ላስተምርህ አለው።

በቅንጡ አዳሪ ትምህርት ቤት ካቋረጠበት 6ኛ ክፍል ለመቀጠል ወደ እውቁ ሪክስ ኢንስቲቲዩት አምርቷል።

የላይቤሪያው ፕሬዝደንት ጆርጅ ዊሃ 10ሺህ ዶላር ሸልመውታል። አንድ የመገናኝ ብዙሃን ባለቤት ከአድማጮቹ ገንዘብ አሰባስቦ ለኢማኑኤል በምስጋና መልክ ገንዘብ ሰጥተዋል። ገንዘቡ የተመለሰለትም በአይነት 1500 ዶላር የሚያወጣ እቃ በስጦት መልክ አበርክቷል።

ኢማኑኤል ለታማኝነቱ ይህ ብቻ አይደለም ያገኘው፤ በአሜሪካ የሚገኝ ኮሌጅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ስክሎላርሺፕ እንደሚሰጠው ቃል ገብቶለታል።

ወደ ትምህርት ገበታ

"ወደ ትምህር ቤት በመመለሴ በጣም ደስተኛ ነኝ። ትምህርት ቤቱ ሪክስ በመሆኑ ሳይሆን ትምህርቱ እና ስነ-ስርዓቱ አስደሳች ነው" ይላል ኢማኑኤል።

የ19 ዓመቱ ወጣት ወላጆቹን በሞት ከተነጠቀ በኋላ ነበር የ9 ዓመት ልጅ ሳለ እራሱን እና ቤተሰቡን ለመደገፍ ትምህርቱን ያቋረጠው። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ገና በለጋ እድሜው ሞተር ሳይክል መንዳት ጀመረ።

"ኢማኑኤል ወደ ትምህር ቤት ሲመጣ ክፍል ውስጥ ድምጹ አይሰማም ነበር። ትኩረት እየሰጠነው በጊዜ ሂደት መሻሻል አሳየ" ሲሉ መምህሩ ታምባ ባንጋቦሬ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

'ታማኝ መሆን መልካም ነው'

ኢማኑኤል ሰዎች ገንዘቡን ስለመልስ ለምን እንዳፌዙብኝ ይገባኛል ይላል። ምናልባት ያን ገንዘብ ለራሱ ቢያውለው በሕይወቱ ብዙ ለውጥ ሊያመጣለት እንደሚችል የሚናገረው ኢማኑኤል፤ "አሁን ያገኘሁትን ያክል ግን ለውጥ አያመጣልኝም ነበር" ይላል።

"ወላጆቼ ታማኝ እንድሆን ስላስተማሩኝ አመሰግናቸዋለሁ" ብሏል።

"ለወጣቶች የምለው ነገር፤ ታማኝ መሆን መልካም ነው፤ የእናንተ ያልሆነውን ነገር አትወስዱ" ሲልም መልዕክቱን አስተላልፏል።