የቢቢሲ ዩክሬን አርታኢ የጦርነት ማስታወሻ

ይህ ጦርነት ከጀመረ ወደ ሁለተኛ ሳምንት እየገባን ነው ማልቀስም አቁሜያለሁ።
ቀኔን የምጀምረው የምሽት ዜናዎችን እያነበብኩና በመላው ዩክሬን የደረሱ አዳዲስ ፍንዳታዎችን እየቆጠርኩ ነው።
ከሁለት ቀናት በፊት ስነቃ አባቴ በሚኖርበት ኪዬቭ ትላልቅ የሮኬት ጥቃቶች ሪፖርቶችን መድረሱን አወቅኩ። ድፍረት አግኝቼ እሱ እና ባለቤቱ ደህና መሆናቸውን ለመጠየቅ 10 ደቂቃ ፈጅቶብኛል። ደህና ነበሩ። ትልቅ እፎይታ ተሰማኝ።
በኪዬቭ የደረሱ አሰቃቂ ጉዳቶችን እና የሩስያ ታንኮችን በከተማው ዙሪያ በሚገኙ መንደሮች ስመለከት እነዛ ጓደኞቻችን የነበሯቸው ጥንታዊ ቤቶች እና ጸጥታው ትውስ ይለኛል። አስታውሳለሁ ከልጆቻችን ጋር እንጠይቃቸው ነበር። በምቹዎቹ ወንበሮች ላይ ተቀምጠን ምግቡን እየተቋደስን ወይን እንጠጣ ነበር። አንዳንዶቹ ከተሞች አሁን በከባዱ ውጊያ ወድመዋል።
በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ ዓይኖቼን እንባ የሞላው ነገር በኪዬቭ ስላሉ ዝግጅቶች በተለያዩ መተግበሪያዎች የተላለፈው መልዕክት ነው። ኮንሰርቶች እና ኤግዚቢሽኖች በዚያ ቀን ከማይደረጉ ነገሮች ዝርዝር ውስጥ ነበሩ። ሳስባቸው ያለፈው ሕይወት አካል ነው የሚመስሉኝ። እነዚህ መተግበሪያዎች የተለያዩ አይነት መረጃዎችን መስጠት ጀምረዋል። ስለ አየር ጥቃቶች፣ ስለሱፐርማርኬቶች የምግብ ዝርዝር እና መድሃኒት ስላላቸው ፋርማሲዎች ያሳውቃሉ።
እናቴ ከራሷ ይልቅ ለውሻዋ እና ለድመቷ ምግብ እንዴት እንደምታገኝ ትጨነቃለች። ባለፈው ቀን ሁለት ዳቦ መግዛቷን ልትነግረኝ በደስታ ተሞልታ ደወለችልኝ። ይህቺ ምግብ በብዛት የሚገኝባት ከተማ ነበረች።
ከተቃጠሉት የሩሲያ ታንኮች ምስል የበለጠ ይህ ለእኔ አስደንጋጭ ነው። የምግብ እጥረት እና ባዶ መደርደሪያዎች የምንጋፈጣቸው እውነታዎች ናቸው። ሰዎች የት ምን መግዛት እንደሚችሉ መረጃ ያጋራሉ። አንዳንድ ሱቆች እጥረት ቢያጋጥማቸው ለተቸገሩ ሰዎች ግን ሁልጊዜም በቂ ነው። ምግብ ቤቶች ለወታደሮች፣ ቤታቸው ለወደመባቸው ወይም ድጋፍ ለሚሹ ሰዎች ምግብ በነጻ ያዘጋጃሉ።
የ10 ዓመት ልጄ ወደ ትምህርት ቤት አይሄድም። የበይነ መረብ ትምህርት እንኳን አያገኝም። አንዳንድ መምህራን በኪዬቭ ሲቆዩ ሌሎቹ ደግሞ ሸሽተዋል። አብረውት የሚማሩት ወደ ገጠር ወይም ወደ ውጭ ሃገር ተሰደዋል። ለመጫወት እና ለዩክሬን የሚዋጉ የበይነ መረብ ጠላፊዎችን በመምሰል ዙም በተሰኘው መተግበሪያ ላይ ያወራሉ። በመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያው ላይ ካዋቀሩት መልዕክቶች አንዱ "የጦርነት ጉዳዮች" የሚል ነው።
ዩክሬናውያን በየቀኑ ባሉበት የመቆየት ወይም የመሰደድ ውሳኔ ያጋጥማቸዋል።
በጦርነቱ የመጀመሪያ ሳምንት ብቻ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሻንጣቸውን ሸክፈው ዩክሬንን ለቀው ስደተኞች ሆነዋል። ቁጥሩ በፍጥነት እያሻቀበ ነው። ብዙዎች ግን ቢያንስ ለጊዜው ለመቆየት ወስነዋል። ታዋቂ ዘፋኞች፣ አርቲስቶች እና ስፖርተኞች ጦሩን ለመቀላቀል ተመዝግበዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዩክሬናውያን በጣም የተቸገሩትን ለመርዳት በጎ ፈቃደኞች ሆነዋል።
ዩክሬናውያን አንድ ትልቅ ቤተሰብ የሆኑ ይመስላል። በዚህም እያንዳንዱ አባል በሚችለው መንገድ ለመርዳት እየሞከረ ይመስላል። መዋጋት የሚችሉት ይዋጋሉ፤ ማብሰል የሚችሉ ያበስላሉ፤ ማድረስ የሚችሉት ያደርሳሉ። የሩሲያ ጦር መጀመሪያ በተቆጣጠራት ኬርሶን እግርና ጣት የሌላቸው አዛውንት በጎ ፈቃደኞች መሆናቸውን የሚገልጽ ልብ የሚሰብር ታሪክ ሰማሁ።
አሁን እያንዳንዱ ከተማ መግቢያ እና መውጫ ላይ ከአሸዋ ከረጢት፣ ከብሎኬት እና ከተቆረጡ ዛፎች የተሠሩ የፍተሻ ኬላዎች አሉት። የታጠቁ ሰዎች ማለትም ከኪዬቭ የሸሹ ወጣት ባለሙያዎች፣ የየአካባቢዎቹ ገበሬዎች ወይም ጡረተኞች የሚገቡትን ሰዎች ሰነዶች ያረጋግጣሉ።
እኔ ባለሁበት መንደር ሁለት የፍተሻ ኬላዎች አሉ። የአካባቢው ሰዎች እየተፈራረቁ በቀን ለ24 ሰዓት ጥበቃ ያደርጋሉ። ጠመንጃዎች ሲኖራቸው አንዳንዶቹ ቢላዋ ወይም መጥረቢያ ይይዛሉ። ማህበረሰቦቻቸውን ባላቸው ነገር ሁሉ ለመጠበቅ ዝግጁ ናቸው።
ይህ የአንድነት ስሜት በዩክሬናውያን ዘንድ ጠንካራ ሆኖ አያውቅም። ሃገሪቱ የድል ተስፋን እየፈጠረ እንዳለ ቀፎ በእንቅስቃሴ የተሞላች ናት።












