ቻይና የምጣኔ ሀብት እድገቷ ዝግ ስላለ የወለድ መጠን ቀነሰች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቻይና ባልተጠበቀ ሁኔታ የወለድ መጠኗን ቀነሰች። ውሳኔው ከሁለት ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያው ነው።
ቻይና ውሳኔውን ያሳለፈችው የምጣኔ ሀብት እድገቷ በመቀዛቀዙ ዝግ ስላለ ነው ተብሏል።
ካለፈው ዓመት አንጻር ባለፉት 3 ሳምንታት ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት 4 በመቶ መጨመሩን ብሔራዊ ስታትስቲክስ አስታውቋል።
እድገቱ ከተገመተው የተሻለ ቢሆንም ካለፈው መንፈቅ አንጻር ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል።
የምጣኔ ሀብት እድገቱ ዝግ ማለቱን የሚያሳየው ታኅሣሥ ላይ የሸቀጥ ሽያጭ ወደ 1.7 በመቶ ማሽቆልቆሉ ነው።
በአጠቃላይ የቻይና እድገት ሲታይ ግን የ8.1 በመቶ እድገት ታይቷል።
ቤይጂንግ ከ6 በመቶ በላይ እድገት ይመዘገባል ብላ ገምታ ነበር።
ባለፈው አንድ ዓመት የታየው መቀዛቀዝ ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር እንደሚያያዝ የምጣኔ ሀብት ተንታኞች ይናገራሉ።
የኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒቱ ዩ ሱ እንደሚሉት፤ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርቱ የተሰላው የኦሚክሮን ዝርያ ያደረሰው ተጽዕኖ ሳይሰላ ነው።
የቻይና ብሔራዊ ባንክ ምጣኔ ሀብቱን ለማነቃቃት ሲል የወለድ መጠኑን መቀነሱን ገልጿል።
ይህ ውሳኔ ቻይናን ከሌሎች አገሮች ብሔራዊ ባንኮች ወደኋላ ያስቀራታል።
የአሜሪካ ፌደራል ሪዘርቭ የወለድ መጠኑን በዚህ ዓመት ሦስት ጊዜ የመጨመር ዕቅድ እንዳለው አስታውቋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ባንክም የዋጋ ግሽበትን ተከትሎ ባለፈው ወር ወለዱን ጨምሯል።
በቤይጂንግ ነጋዴዎች ላይ እየደረሰ ያለው ጫና የቻይና ምጣኔ ሀብት ላይ ጉዳት ሳያሳድር እንዳልቀረ ይነገራል።
በቻይና የእዳ ቀውስ ውስጥ የገቡ ባለሀብቶች በመብዛታቸው ሳቢያ ኢንቨስትመንት ተቀዛቅዟል።
ይህ ቤት አልሚዎች ከባንክ መበደር የሚችሉት የገንዘብ መጠን ላይ ገደብ ከተጣለ በኋላ የመጣ ቀውስ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ቻይና ወረርሽኙ በተቀሰቀሰበት ወቅት እንደነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ መጣል መጀመሯም ገበያውን አፍዝዞታል።
በዚህ የተነሳም ሸማቾች አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል።
ከተፈጠረው ውጥንቅጥ ለመውጣት ሲል ነው የቻይና ብሔራዊ ባንክ የወለድ መጠንን ለመቀነስ የወሰነው።
በእርግጥ ቻይና ትልልቅ ንግዶችን የመደገፍ ዕቅድ የላትም። የወረርሽኙ ስርጭት እጅግ ስለሚያሰጋት የእንቅስቃሴ ገደብ የማንሳት ፍላጎትም አላሳየችም።












