ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ አሉ ያሏቸውን ችግሮች አጥብቀው ተቹ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ

የፎቶው ባለመብት, Etv

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፉት ሁለት ቀናት ከካቢኔያቸው ጋር ባደረጉት ውይይት የአገሪቱን የፍትሕ ሥርዓት አጥብቀው ተችተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ከካቢኔ አባላቶቻቸው ጋር ባደረጉት የ100 ቀናት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ላይ "የፍትሕ ተቋማት በገንዘብ ካልተደለሉ በግል ቂም ይደለላሉ" ካሉ በኋላ፤ "አንድ ዳኛ በደም የሚያስብ ከሆነ፣ አንድ ዳኛ በእውቂያ የሚያስብ ከሆነ ገንዘብ ቢቀበልም ባይቀበልም ሙሰኛ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ፍርድ ቤትን፣ ዐቃቤ ሕግን እንዲሁም ፖሊስን አጠቃለው የወቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "እኛ ስለፍትሕ ልናወራ አንችልም። ብዙ ሩቅ ነን [ከፍትሕ] በብዙ ማስረጃ ልከራከራችሁ እችላሁ። ስለ ፍትሕ ልናወራ አንችልም" ሲሉ ለካቢኔ አባላቶቻቸው የተናግሩት በብሔራዊው ቴሌቪዝን ላይ ቀርቧል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ የፍትሕ ሥርዓቱ መሻሻል እንዳለበት ማሳያ አድርገው ያቀረቡት የጦርነቱን መጀመር ተከትሎ በቁጥጥር ሥር ስለዋሉ የትግራይ ተወላጆች ጉዳይን ነው።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ "የትግራይ ተወላጅ ተብለው በተለያየ ጉዳይ የሚጠረጠሩ እና በጥቆማ የሚታሰሩ ሰዎች 70፣ 75፣ 80 ዓመት የሆናቸው ስኳር እና ግፊት ያለባቸውን ሰዎች ወስዶ ማጎር ለኢትዮጵያ ከመቆርቆር እና ኢትዮጵያ ላይ ችግር እንዳይመጣ ከመፈለግ አይደለም። ሃብታም ሃብታሙን ማደን ሌብነት ነው።። ይሄ ለእኛ አይጠቅምም" ሲሉ ተደምጠዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ መሰል አሰራር ጥቅም የለውም ያሉ ሲሆን፤ ". . . በርካታ ሰዎች ካለ አግባብ ይታሰራሉ። አይጠቅመንም። ይህንን አንዳንዴ ፖሊስ፣ አንዳንዴ ዐቃቤ ሕግ፣ አንዳንዴ ፍርድ ቤቱ ያደርገዋል። ሙሉ የፍትሕ ሥርዓቱ ወይ ብር ይቀበላል፣ ወይ ደም፣ ወይ እምነት ያታልለዋል" ብለዋል።

ይህ የጠቅላይ ሚንስትሩ ትችት የተሰማው የአዲስ አበባ ፖሊስ "ከህወሓትት ጋር ግንኙነት አላቸው" በሚል ታስረው የነበሩ ሰዎችን መልቀቅ ጀምሬያለሁ ካለ በኋላ ነው።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ትናንት ሐሙስ ባወጣው መግለጫ "የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ በሚሰጥ መመሪያ መሰረት ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው ከሚገኙ ተጠርጣሪዎች መካከል በድርጊታቸው የተወሰኑት በዋስ ከእስር እንዲፈቱ ተደርጓል" ሲል ገለጿል።

የመዲናዋ ፖሊስ የተቀሩት በቁጥጥር ስር የሚገኙ ግለሰቦች "እንደ ድርጊታቸው ክብደትና ቅለት እየታየ ወደፊት ይለቀቃሉ" ያለ ሲሆን፣ በዋስ ተለቅቀዋል ያላቸው ግለሰቦች ደግሞ ወደፊት እንደ ጥፋታቸው በሕግ እንደሚጠየቁ እና በሕግ አካላት ጥሪ ሲደረግላቸው የመቅረብ ግዴታ እንዳለባቸው አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስን ምን ያክል ሰዎችን እንደለቀቀ፣ ምን ያክሉ አሁን በእስር እንደሚገኙ እና ክስ የተመሰረተባቸው ሰዎችን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ለመጠየቅ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ፖሊስ በመግለጫው በእስር ላይ ከቆዩት መካከል "በድርጊታቸው ተጸጽተው ይቅርታ የጠየቁትን፣ ከፍተኛ ወንጀል ያልፈጸሙ እና ከእሥር ቢወጡም ለከተማዋ ስጋት የማይሆኑ" በሚል በጥንቃቄ ተለይተዋል ያለ ሲሆን፣ የተፈቱትም በዋስ መሆኑን አመልክቷል።

"የታሰሩ ሰዎች መለቀቃቸው የሚያበረታታ ነው"

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ ባለፉት ጥቂት ቀናት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሴቶች፣ አዛውንቶች እና የተለያየ የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች መለቀቃቸውን ገልጿል።

ኮሚሽኑ አክሎም የፖሊስን እርምጃ የሚያበረታታ ተግባር ነውም ብሏል።

ኮሚሽኑ በመግለጫው ላይ በአዲስ አበባ እና በሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ተመሳሳይ እርምጃ እንዲቀጥል ጠይቋል።

"አሁንም በእስር ላይ የሚገኙ የጋዜጠኞች ጉዳዮችን ጨምሮ የምርመራ ሂደቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ እና የእስር ሁኔታ እንዲሻሻል ብሎም ሰዎች የቤተሰብ አባሎቻቸው ያሉበትን ቦታ እና ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲነገራቸው እናሳስባለን" ሲልም ጥሪውን አቅርቧል።

ኮሚሽኑ ከዚህ በፊትም የእስረኞች አያያዝን እንዲሁም ፍርድ ቤት በነጻ ከለቀቃቸው በኋላ በእስር ላይ ስለሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን በሚመለከት መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።