ራልፍ ራንኚክ፡ አዲሱ የማንቸስተር ዩናይትድ ጊዜያዊ አሠልጣኝ ማናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእንግሊዙ እግር ኳስ ክለብ ማንችስተር ዩናይትድ ራልፍ ራንኚክን በጊዜያዊ አሠልጣኝነት ሊቀጥር ከጫፍ ደርሷል።
የ63 ዓመቱ ጀርመናዊ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ቡድኑን ማሰልጠን የሚያስችላቸውን ውል ለመያዝ ከጫፍ ደርሰዋል።
ራልፍ ቀጣይ እሑድ ዩናይትድ ከቼልሲ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ በሥራ ፈቃድ ምክንያት መታደም ባይችሉም ከሚቀጥለው ጨዋታ በኋላ ኃላፊነት ይወስዳሉ።
ዩናይትድ ከራልፍ ጋር ስምምነት ቢደርስም አሁን በስፖርትና ዕድገት ኃላፊነት ከሚሠሩበት ሎኮሞቲቭ ሞስኮው ጋር መስማማት ይቀረዋል።
ማንችስተር ዩናይትድ ለሶስት ዓመታት ያክል ቡድኑን አሠልጥኖ ውጤት ማምጣት ካልቻለው ኦሌ ጉናር ሶልሻዬር ጋር ከተለያየ በኋላ ነው ራልፍ ለመቀጥር የተስማማው።
ራንኚክ ከሻልከ ጋር በፈረንጆቹ 2011 የጀርመን ዋንጫ ያነሱ ሲሆን አርቢ ሊፕዚክን ደግሞ ከሁለት ዓመት በፊት ለፍፃሜ አድርሰዋል።
ጀርመናዊው አሠልጣኝ በ2010/11 የእግር ኳስ ዘመን ሻልከን ይዘው ለቻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍፃሜ ቢደርሱም ከዩናይትድ ጋር በነበራቸው የደርሶ መልስ ጨዋታ 6-1 ተሸንፈው መውደቃቸው አይዘነጋም።
ማንችስተር ዩናይትድ በዘንድሮው ፕሪሚዬር ሊግ ሰንጠረዥ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በ1999 ቻምፒዬንስ ሊግ ፍፃሜ ለዩናይትድ ዋንጫ ያስገኘች ጎል ያስቆጠረው ሶልሻዬር ከአሠልጣኝነቱ የተሰናበተው በዋትፈርድ 4-1 ከተሸነፈ በኋላ ነው።
የክለቡ የቀድሞ አማካይና የኦሌ ረዳት አሠልጣኝ የነበረው ማይክል ካሪክ ቡድኑን በጊዜያዊነት እየመራ ይገኛል።
በማይክል ካሪክ የተመራው ዩናይትድ በቻምፒዬንስ ሊግ የምድብ ጨዋታ ቪላሪያን 2-0 በመርታት የምድቡ አንደኛ ሆኖ ማለፉን አረጋግጧል።
ራንኚክ፤ ስቱትጋርት፣ ሃኖቨር፣ ሆፈንሃይም፣ ሻልከና ሊፕዚክን አሠልጠናዋል። በዚህ በጀርመን እግር ኳስ ስማቸው ተደጋግሞ ይነሳል።
ከዩናይትድ ጋር በሳምንቱ መባቻ ንግግር ያደረጉት ራንኚክ ከቡድኑ ጋር የስድስት ወራት የጊዜያዊ አሠልጣኝነት ውል የሚገቡ ሲሆን ቡድኑ ቋሚ አሠልጣኝ ከቀጠረ በኋላም በቴክኒካል አባልነት ሊቆዩ ይችላሉ።
የእግር ኳስ ተንታኞች ዩናይትድ ሰውዬውን ማምጣቱ ተገቢ ነው፤ ቋሚ አሠልጣኝ ፈልጎ ለመቅጠርም ዕድል ይሰጣል ይላሉ።
ሞሪሲዮ ፖቼቲኖ የዩናይትድ ቀዳሚ የአሠልጣኝ ምርጫ እንደሆነ እየተነገረ ነው። ነገር ግን ከፒኤስጂ ጋር ያልተቋጨ ውል ያለው ፖች ወዲያውኑ ላይገኝ ይችላል የሚል ስጋት አለ።
ዩናይትድ እሑድ አመሻሹን ከቼልሲ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ በማይክል ካሪክ እየተመራ እንደሚፋለም ታውቋል።
ራንኚክ ከአሁኑ የቼልሲ አሠልጣኝ ቱኽል ጋር አብረው የሠሩ ሲሆን የሊቨርፑሉ አሠልጣኝ ዩርገን ክሎፕም የሳቸው የጨዋታ ፍልስፍና ውጤት ናቸው ይባላል።












