ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሱዳን ውስጥ በማኅበረሰቦች መካከል በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ 43 ሰዎች ተገደሉ
በሱዳን ዳርፉር ግዛት ውስጥ በሁለት ማኅብረሰብ አባላት መካከል በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ 43 ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።
ግጭቱ የተከሰተው በደርፉር ግዛት ውስጥ ባሉ አረብ አርብቶ አደሮች እና የሚሴሪያ ጄቤል ጎሳ አባላት በሆኑ አርሶ አደሮች መካከል ነው።
የመንግሥታቱ ድርጅት ግጭቱ ለቀናት መቀጥሎ 40 መንደሮች መቃጠላቸውን እና መዘረፋቸውን ገልጿል።
በግጭቱ ሳቢያ ከተገደሉት ሰዎች በተጨማሪ ሕጻናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች አስካሁን የደረሱበት አለመታወቁ ሪፖርት ተደርጓል።
የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ኃይል ዳርፉርን ለቆ ከወጣ በኋላ በግዛቲቱ ባሉ ማኅበረሰቦች መካከል ተደጋጋሚ ግጭቶች ይከሰታሉ።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከአንድ ወር በፊት የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ በመላዋ አገሪቱ በተለይም በዋና ከተማዋ ተቃውሞና ግጭቶች ሲካሄዱ የቆዩ በመሆናቸው በዳርፉር ያለው ችግር ትኩረት እንዳያገኝ አድርጎታል።
ግጭት የማያጣት ዳርፉር
እንደ ተመድ መረጃ ከሆነ ዳርፉር ወደ 80 የሚጠጉ ጎሳዎችን ይዛለች።
ከሱዳን መዲና ካርቱም በስተ ምእራብ የምትገኘው ዳርፉር ተደጋጋሚ ግጭቶችን ታስተናግዳለች። የግጦሽ መሬት እና የውሃ ቦታዎች የይገባኛል ጥያቄ እንዲሁም የቁም እንስሳት ዝርፊያ በተለያዩ ማኅብረሰብ አባላት መካከል ለሚፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት ናቸው።
በጎረቤት አገር ቻድ ያለው ጦርነትን ወደ ዳርፉር አነስተኛ የጦር መሳሪያዎች እንዲገቡ ማስቻሉ፤ በማኅብረሰብ አባላት መካከል በሚደረጉ ግጭቶች የተጎጂዎች ቁጥር ከፍ እንዲል ምክንያት ሆኗል።