ናይጄሪያ ውስጥ 22 ፎቅ ያለው ሕንፃ ተደርምሶ ሰዎች ሞቱ

በናይጄሪያዋ ሌጎስ ከተማ 22 ፎቆች ያሉትና በመገንባት ላይ ያለ ሕንፃ ተደርምሶ አደጋ በማድረሱ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ሰዎችን ለማትረፍ ርብርብ ላይ ናቸው።

እስካሁን አራት ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ በርካቶች የገቡበት አልታወቀም።

ፍርስራሽ እየቆፈረ ሰዎችን የሚያድን ማሽን እንዲሁም የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችና የአካባቢው ነዋሪዎች ነብስ ለማዳን እየተሯሯጡ ነው።

አራት ሰዎች ከፍርስራሽ ሲሚንቶና ከተጣመመ ብረት መሃል ሆነው በሕይወት ተገኝተዋል።

ሕንፃው በምን ምክንያት እንደተደረመሰ እንዲሁም ሲደረመስ ምን ያህል ሰዎች ውስጡ እንደነበሩ እስካሁን ግልፅ አይደለም።

የአካባቢው ባለሥልጣናት ሕንፃው በምን ምክንያት ሊወድቅ እንደቻለ መርምረው ውጤቱን ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።

የፕሬዝደንት ሙሐሙዱ ቡሐሪ ልዩ አማካሪ የሆኑት ፌሚ አዴሲኛ "ፕሬዝዳንቱ በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ሰዎች ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል" ብለዋል።

አልፎም ፕሬዝደንቱ የአደጋ ጊዜ ሥራው እንዲጣደፍ ለባለሥልጣናት ትዕዛዝ ሰጥተዋል ሲሉ አማካሪው ተናግረዋል።

ኢኮይ ገበያ አካባቢው ሲገነባ የነበረው ሕንፃ ተደርምሶ የወደቀው በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት ስምንት ሰዓት ከ45 ደቂቃ አካባቢ እንደነበር ታውቋል።

360 ድግሪ ታወርስ የተሰኘው የገበያ ማዕከል አካል የሆነው ሕንፃ ቅንጡ አፓርትመንቶችን ይይዛል ይላል ሕንፃውን የሚሠራው ተቋራጭ ድርጅት።

የተቋራጩ ድረ-ገፅ ሕንፃው ከተደረመሰ በኋላ አገልግሎት መስጠቱን አቁሟል።

ሕንፃውን የሚገነባው ፎርስኮር ሆምስ የተባለው ድርጅት በዩናይትድ ኪንግደም፣ ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በሌሎች የናይጄሪያ ክፍሎች ፎቆች ይገነባል።

የ41 ዓመቱ የግንባታ ሠራተኞ ኤሪክ ቴቴህ አሶሲዬትድ ፕሬስ ለተሰኘው የዜና ወኪል ሕንፃው ድንገት ሲወቅድ አብዛኛዎቹ ሰዎች 'ኤክስካቫታር' እየጠበቁ ነበር ሲል ተናግሯል።

"እኔና ወንድሜ አምልጠናል። ነገር ግን በርካታ ሰዎች አሁንም ውስጥ ናቸው። ከ100 በላይ ሰዎች" ብሏል።

ከተደረመሰው ሕንፃ ተቃራኒ ይሠራ የነበረ ግለሰብ "ድምፅ ሰምቼ በመስኮት ወጥቼ ስመለከት ሕንፃው አንድ በአንድ እየተናደ ሲወድቅ ነበር" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ኤፒ የዜና ወኪል እንደሚለው የሌጎስ ምክትል ገዢ የሆኑት ፌሚ ሃምዛት ፍርስራሹን ለመጎብኘት በሄዱ ወቅት የአደጋ ጊዜ ሥራው በጊዜ አልተጀመረም ያሉ የአካባቢው ሰዎች ከበዋቸው ነበር።

ሌጎስ ውስጥ በቅርብ ዓመታት የሕንፃ መደርመስ ዜና መሰማት የተለመደ ሆኗል።

ከሁለት ዓመት በፊት የንግድ ማዕከል በሆነችው ሌጎስ አንድ ትምህርት ቤት ተደርምሶ 10 ሰዎች ሞተው ነበር።

ከሰባት ዓመታት በፊት ደግሞ ስድስት ፎቆች ያሉት አንድ ሕንፃ በርካታ አማኞች ስብከት ለመከታተል ወጥተውበት በመደርመሱ 116 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።