የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከሥልጣን የተወገዱትን የሱዳኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አነጋገሩ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከሥልጣን የተወገዱት የሱዳን ሲቪል ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ተከትሎ በስልክ ማነጋገራቸው ተገለጸ።
ሰኞ ዕለት በሱዳን የተከሰተውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ በቁጥጥር ስር ውለው ነበር።
ከሥልጣን የተወገዱት ጠቅላይ ሚኒስትር በመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን ቤት የቆዩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል።
ጄኔራሉ "ለራሳቸው ደኅንነት" ሲባል በቤታቸው አስጠልለዋቸው እንደነበር ተናገረዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ አንቶኒ ብሊንከን የጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክን መፈታት በደስታ እንደሚቀበለው እና የሱዳን ታጣቂ ኃይሎች ባለፉት 24 ሰዓታት የታሰሩትን የሲቪል መሪዎች በሙሉ እንዲፈቱ በድጋሚ ጥሪ አቅርቧል።
የጦር ኃይሉ ስልጣንን በኃይል መቆጠጣሩን ተከትሎ የተነሳው የአደባባይ ተቃውሞ በዋና መዲናዋ ካርቱም ሕዝቡ በሰላማዊ ሰልፍ እና ዋና መንገዶችን በመዝጋት እስከ ምሽቱ ድረስ ቀጥሏል።
ቀደም ሲል ጄኔራል አብዱልፈታህ አል-ቡርሐን የፖለቲካ ቡድኖች ሰላማዊ ሰዎችን በፀጥታ ኃይሎች ላይ ሊያነሳሱ ሞክረዋል በሚል የመፈንቅለ መንግሥቱን ምክንያታዊነት ለማስረዳት ሞክረዋል።








