በምሥራቅ ወለጋ እና በሆሮ ጉዱሩ በቂ የፀጥታ ኃይል እንዲመደብ ኢሰመኮ ጠየቀ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሸን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል፣ በምሥራቅ ወለጋ እና በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች እየተስፋፋ የመጣው ጥቃት ወደ ብሔር ተኮር የእርስ በእርስ ግጭት ሊያመራ ስለሚችል፤ የንጹሀን ዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ በቂ የፀጥታ ኃይል እንዲሰማራ ጠየቀ።
ኢሰመኮ ዛሬ ጥቅምት 8/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ በእነዚህ ዞኖች በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በሲቪሎች ላይ የሚጸሙ ጥቃቶች እየተስፋፋ ከመምጣቱ ባሻገር ጥቃቱ ባህሪውን እየቀየረ ወደ ብሔር ተኮር የእርስ በእርስ ግጭት ሊያመራ ይችላሉ ብሏል።
ስለዚህም መንግሥት በአፋጣኝ በቂ የፀጥታ ኃይሎችን በቋሚነት በአካባቢዎቹ እንዲያሰማራ ኮሚሽኑ ጠይቋል።
ባለፈው ሳምንት ግጭት የተከሰተባቸው ኪረሙ ወረዳን ጨምሮ በተለያዩ የምሥራቅ ወለጋ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች በአስጊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የገለጸው ኢሰመኮ፤ "ወደ ወረዳው የሚወስዱ የተዘጉ መንገዶችን ማስከፈትን ጨምሮ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ከፌደራሉ ኃይሎች ጋር ሊቀናጁ ይገባል" ብሏል።
ባለፈው ሳምንት በኪራሙ ወረዳ፣ ሀሮ ከተማ ግጭት የተነሳው የኦሮሚያ ልዩ ኃይል "ለሌላ ሥራ" አካባቢውን ለቆ ከወጣ በኋላ እንደሆነ ከክልሉ የፀጥታ ኃላፊዎች መረጃ እንዳገኘ ኮሚሽኑ አመልክቷል።
ኢሰመኮ በመግለጫው "በሀሮ፣ አዲስ ዓለም ቀበሌ ከመስከረም 30/2014 ዓ. ም. ጀምሮ ሲቪል ሰዎች በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መገደላቸውን የፀጥታ ኃይሎች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል" ብሏል።
ይህንን ግድያ ምክንያት በማድረግም "በኢመደበኛ ሁኔታ የተደራጁ የተወሰኑ የአካባቢው እና የአጎራባች ክልል ነዋሪዎች" በርካታ ንጹሀን ዜጎችን እንደገደሉ ኢሰመኮ አስታውቋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እንዳሉት፤ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች አንድ አካባቢን ለቅቀው መሄዳቸውን ተከትሎ የሚፈጸሙ ጥቃቶች "እጅግ አሳሳቢ መሆናቸውን" ከዚህ ቀደምም ኮሚሽኑ ለመንግሥት አስታውቋል።
በአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶች ብሔር ተኮር ወደሆነ የእርስ በእርስ ግጭት እንዳይለወጡ ለግጭት እና ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ላይ በቂ የፀጥታ ኃይል በቋሚነት እንዲመደቡ ዋና ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።
የአካባቢው ሰላም እና ደኅንነት ሙሉ በሙሉ እስከደሚረጋገጥ ድረስ በቂ የፀጥታ ኃይል እንዲመደብ የጠየቁት ዶ/ር ዳንኤል "መንግሥት የሁሉንም ነዋሪዎች ደኅንነት የማስጠበቅ እና ከጥቃት የመከላከል ግዴታ እና ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል" ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ነሐሴ 12/2013 ዓ.ም. በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን፣ በኡሙሩ ወረዳ የአካባቢው ነዋሪዎች በሆኑና "እራሳቸውን ከጥቃት እንዲከላከሉ" በሚል መሣሪያ እንዲታጠቁ በተፈቀደላቸው የአካባቢው ነዋሪዎቸ በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ንጹሀን መገደላቸውን ኢሰመኮ በመግለጫው አስታውሷል።
"እነዚህ ሁሉ ጥቃቶች እና ግድያዎች የብሔር ማንነትን መሠረት አድርገው አንድ ጊዜ በአማራ ብሔር ተወላጆች፣ ሌላ ጊዜ በኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ላይ የሚፈጸሙ ብሔር ተኮር ጥቃቶች በመሆናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በሆኑ በሁለቱ ብሔር ተወላጆች መካከል ከፍተኛ ውጥረት እና የእርስ በእርስ ግጭት ስጋት ተፈጥሯል" ሲልም በመግለጫው አሳስቧል።
ግጭቶቹን በመሸሽ ከምሥራቅ ወለጋ ሊሙ ወረዳ፣ ጉደያ ቢላ ወረዳ፣ ኪረሙ ወረዳ፣ ሌቃ ዱለቻ ወረዳ፣ በዲጋ ወረዳ፣ እና ከሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ኡሙሩ ወረዳ በአጠቃላይ ከ43139 በላይ ሰዎች ተፈናቅለው እንደሚገኙም ተገልጿል።
ወደእነዚህ አካባቢዎች የሚወስዱ መንገዶች ዝግ በመሆናቸው እንዲሁም በአካባቢው ያለው ውጥረት አሁንም ባለመርገቡ ምክንያት ሰዎች መሠረታዊ አቅርቦቶችን እና ሕክምና ለማግኘት እንደተቸገሩ ኢሰመኮ አመልክቷል።
ዋና ኮሚሽነሩ ዶ/ር ዳንኤል፤ "በግጭቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ሰዎች አፋጣኝ የሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ ሲሉ አሳስበዋል።
በኦሮሚያ ክልል፣ በምሥራቅ ወለጋ ዞን፣ በኪረሙ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው ሀሮ ከተማ መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም በተከሰተው ግጭት የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን እና ንብረት መውደሙን የዓይን እማኞች እና አንድ የክልሉ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ገለጸው ነበር።
ከተፈጸመው ጥቃት ጋር በተያያዘ የ15 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን የኦሮሚያ ክልል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ የተናገሩ ሲሆን ሌሎች ግን ህይወታቸው የጠፋው ሰዎች ቁጥር ከተጠቀሰው በላይ እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል።












