አስተያየት፡ ለምን በትግራይ ክልል ረሃብ ተከሰቷል ተብሎ አልታወጀም?

በጦርነቱ የተፈናቀሉ ወጣቶች፣ መቀለ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, AFP

    • ፀሐፊ, አሌክስ ደ ዋል*
    • የሥራ ድርሻ, የአፍሪካ ጉዳዮች ተንታኝ

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነቱ ከተጀመረ አንድ ዓመት ሊሞላው በተቃረበበት ጊዜ በትግራይ ክልል ውስጥ መጠነ ሰፊ ረሃብ ቢከሰትም ዓለም አቀፍ የእርዳታ ባለሥልጣናት ችጋር ተከስቷል ብለው ለማወጅ አልደፈሩም።

ማሳሰቢያ፡ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የሚገኝ ፎቶ አንዳንድ ሰዎችን ሊረብሽ ይችላል።

በመቀለ ከተማ ከሚገኘው የአይደር ሆስፒታል የወጣ ሪፖርት እንደሚያመለክተው ህጻናት በረሃብ ሳቢያ እየሞቱ ነው።

የሆስፒታሉ ዶክተሮች ያነሷቸው ፎቶዎች የደረት አጥንታቸው የሚታይና ሆዳቸው ያበጠ ህጻናት በከባድ የምግብ እጥረት የተጎዱ መሆናቸውን ያሳያሉ። በሆስፒታሉ ለተወሰኑ ሳምንታት የሚሆን አስቸኳይ ለህክምና የሚሆን የምግብ አቅርቦት ስላለ እነዚህ ህጻናት እድለኞች ናቸው።

በትግራይ መንደሮች ውስጥ ያለው ሁኔታ በጣም የከፋ ነው። ጦርነቱ ባለፈው ዓመት ከተከሰተ ከሁለት ወራት በኋላ በአዲግራት የሚገኙ የካቶሊክ ጳጳስ ሰዎች በረሃብ ሳቢያ እየሞቱ እንደነበር ተናግረዋል። በሰኔ ወር በአንድ አካባቢ 125 ሰዎች ራቅ ብሎ በሚገኝ መንደር ውስጥ እንደሞቱ ገልጸው ነበር።

ለቀናት በእግራቸው ተጉዘው መቀለ የደረሱ ቤተሰቦች እንደሚናገሩትም ምግብ ባለመኖሩ ለሳምንታት ስራ ስሮችን እየተመገቡ እንደቆዩ ተናግረዋል።

የአይደር ሆስፒታል ዳይሬክተር ዶ/ር ሀየሎም ከበደ ነርሶች ወደ ሥራ ሲመጡ ቀኑን ሙሉ ተመግበው የሚውሉትን ትንሽ ቆሎ ይዘው እንደሚመጡ ይናገራሉ። ልጆቻቸውም በምግብ እጥረት ተጎድተዋል።

ከሰኔ ወር ጀምሮ ባንኮች በመዘጋታቸው ለአራት ወራት ሠራተኞች ደሞዝ አላገኙም። የገንዘብ እጥረት በመኖሩም የሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

ከተፈናቀሉ ህጻናት መካከል ከ20 በመቶ የሚበልጡት በከፋ የምግብ እጥረት ተጠቅተዋል። ቅርቡ በተባበሩት መንግሥት የወጣ መረጃ 79 በመቶ የሚሆኑ ነፍሰ ጡርና የሚያጠቡ እናቶች በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ እንደሆኑ አመልክቷል። ይህም ከ10 ዓመት በሶማሊያ ከተከሰተው ረሃብ በኋላ ያጋጠመ ነው።

በዚህ ሳምንት በአይደር ሆስፒታል እየታከሙ ካሉ በምግብ እጥረት ከተጎዱ ህጻናት መካከል አንዱ

የፎቶው ባለመብት, Ayder Hospital

የምስሉ መግለጫ, በዚህ ሳምንት በአይደር ሆስፒታል እየታከሙ ካሉ በምግብ እጥረት ከተጎዱ ህጻናት መካከል አንዱ

'በረሃብ ሁኔታ ውስጥ'

ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ከወራት በኋላ በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የወጣው መረጃና ካርታ ችግሩ እየተባባሰ 400 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች በከባድ የሰብአዊ ቀውስ ደረጃ ላይ መሆናቸውን አመልክቶ ነበር።

ባለፈው ሰኔ የተባበሩት መንግሥታት ያዋቀረው ኮሚቴ በትግራይ ውስጥ ስላለው የምግብ ዋስትና ሁኔታን በተመለከተ ባሰባሰበው መረጃ መሰረት በክልሉ ከሚካሄደው ውጊያና ከእርዳታ አቅርቦት አንጻር ሊሆን የሚችሉ አራት ሁኔታዎች አቅርቦ ነበር።

የከፋ ባለው ሁኔታ ጦርነቱ ከተባባሰ የእርዳታ አቅርቦቱ በጣም ዝቅተኛ በመሆን ከሚያስፈልገው ከ10 በመቶ በታች ብቻ እንደሚሆንና የባንኮች መዘጋት፣ የመሰረታዊ አቅርቦቶች መስተጓጎል ስለሚያጋጥም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ይቆማሉ ብሎ ነበር። የረሃቡም ሁኔታ ከመስከረም በፊት "ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ" ከፍ እንደሚልም አመልክቷል።

ቴክኒካዊ በሆነ ቋንቋ ሪፖርቱ አስቸኳይ እርምጃ እንደሚያስፈልግ ግዙፍ የሰብአዊ እርዳታ ጥረት ብቻ ሳይሆን ምን አቅርቦት እንደሚያስፈልግና ለማንና የት የሚለውን ለመለየት የሚያስችል ጠንካራ መረጃ ማሰባሰብ እንደሚገባ ገልጿል።

ነገር ግን ምንም የተከናወነ ነገር የለም። በእርግጥ የተወሰኑ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ሠራተኞች ወደ ትግራይ እንዲጓዙ ቢፈቀድም የመገናኛ እንዲሁም የመረጃ ማጠራቀሚያ መሳሪያዎች ሳይቀሩ እንዳይዙ ተከልክለዋል። በተጨማሪም ሲመለሱ በስልኮቻቸው ላይ ያሉ ፎቶዎች ተበርብረዋል።

ቀድሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ረሃብ ሲከሰት ጆናታን ዲምበልቢ፣ ማይክል በርክ እና ሞሐመድ አሚንን በመሳሰሉ ጋዜጠኞች ነበር ይፋ የወጡት። አሁን መንግሥት ጋዜጠኞች ወደ ትግራይ እንዳይገቡ አድርጓል።

በአማራ ክልል የህወሓት ኃይሎች ሚስታቸውንና ልጃቸውን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደገደሉባቸው የሚናገሩት ቄስ ጥፍጡ እጅጉ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በአማራ ክልል የህወሓት ኃይሎች ሚስታቸውንና ልጃቸውን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደገደሉባቸው የሚናገሩት ቄስ ጥፍጡ እጅጉ

የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ውዝግብ

ሰኔ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ትግራይ ውስጥ ረሃብ የለም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። የመንግሥታቱ ድርጅት በበኩሉ ረሃብ "በቅርቡ ሊከሰት ይችላል" ሰዎችም በምግብ እጥረት ምክንያት "መሞት ሊጀምሩ" ይችላሉ ሲል ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለችግሩ የክልሉ ገዢ ፓርቲ የሆነውና በሽብርተኝነት የፈረጀውን ህወሓትን ተጠያቂ ያደርጋል።

የትግራይ ኃይሎች ወደ አጎራባቾቹ የአማራና የአፋር ክልሎች በመግባት የሰብአዊ ቀውስ ፈጥረዋል ሲል መንግሥት ይከሳል። በእርግጥም የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት እንደሚያመለክተው በክልሎቹ አንድ ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ የእርዳታ ድጋፍ ይፈልጋል፤ ግማሽ ያህሉ በጦርነቱ ሳቢያ የተፈናቀሉ ናቸው ብሏል።

አስተማማኝ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ወደ ክልሎቹ የገቡት የትግራይ ኃይሎች የምግብና መድኃኒት አቅርቦቶችን መዝረፋቸውን ያመለክታሉ።

መንግሥት የአማጺያኑ ወደ ፊት መግፋት የሰብአዊ አቅርቦት መስመሮችን ዘግቷል በማለት ይከሳል፤ ቢሆንም ግን ከአፋር በኩል የእርዳታ አቅርቦት በሚጓጓዝበት መስመር ጦርነቶች እንዳልተካሄዱ ይነገራል። የእርዳታ ተቋማት እንደሚሉት ያለው የጸጥታ ስጋት በመንግሥት ሚሊሻዎች ምክንያት ነው ይላሉ።

በተጨማሪም ወደ ትግራይ የሚደርሱት እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ትንሽ ሊሆን የቻለው ወደ ክልሉ መግባት የቻሉት የጭነት መኪኖች በህወሓት ተይዘው ለጦርነት አላማ እየዋሉ በመሆኑ እንደሆነ መንግሥት ይከሳል።

ነገር ግን ይህ ክስ በመረጃ የተደገፈ እንዳልሆነና ተሽከርካሪዎቹ በነዳጅ ችግር ምክንያት ባሉበት እንደቆሙ ተገልጿል።

በሰኔ ወር ላይ የህወሓት ኃይሎች በኢትዮጵያ ሠራዊት ድል ተቀዳጀን ቢሉም መንግሥት ግን ተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከክልሉ እንዳስወጣ ከገለጸ በኋላ፤ ገበሬዎች ማሳቸው ላይ ለመዝራትና የእርዳታ ድርጅቶችም በክልሉ ውስጥ ያለገደብ ለመንቀሳቀስ እድል ተፈጥሯል።

የእርዳታ አቅርቦትን በተመለከተ ያለው ችግር በትግራይ ውስጥ ሳይሆን የሚያስፈልገውን ነገር እዚያ ማድረስ እንደሆነ የረድኤት ድርጅቶች ይናገራሉ።

የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሥልጣናት የችግሩ መነሻ መንግሥት ይከተለዋል ያሉት እንቅስቃሴ የመገደብ ፖሊሲ እንደሆነ በግልጽ ይናገራሉ።

የመንግሥታቱ ድርጅት ሰብአዊ እርዳታ ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ መስከረም ወር መጨረሻ ላይ "ይህ በመንግሥት ሊስተካከል የሚችል ሰው ሰራሽ ችግር ነው" ብለው ነበር።

ከቀናት በኋላ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት በውስጥ ጉዳዬ ውስጥ ጣልቃ ገብተዋል ያላቸውን ሰባት የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሥልጣናትን ከአገሩ እንዲወጡ አድርጓል።

በክፍት በተካሄደው የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የመንግሥትን እርምጃ አውግዘው ኢትዮጵያ ከድርጅቱ ጋር የገባችውን ስምምነት የሚጥስ ነው ብለዋል።

በመንግሥታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴም በሰጡት ምላሽ የድርጅቱ ሠራተኞችን ለህወሓት ወገንተኝነት እንዳላቸው በመግለጽ በርካታ ክሶች ያቀረቡ ሲሆን፣ ባልተለመደ ሁኔታ ዋና ፀሐፊው ለሁለተኛ ጊዜ በሰጡት ምላሽ ለቀረበው ክስ ማስረጃ እንዲቀርብና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተነጋገሩበት ጊዜ ይኸው ርዕስ ተነስቶ ዝርዝር ቢጠይቁም ምላሽ እንዳላገኙ ተናግረዋል።

የቀድሞው የኦቻ ኃላፊ ማርክ ሎውኮክ ከኃላፊነታቸው ከለቀቁ በኋላ ፒቢኤስ ላይ ቀርበው በሰጡት አንድ ቃለ ምልልስ ላይ "የኢትዮጵያ መንግሥት ትግራይን ለማስራብ እየሞከረ ነው?" ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ የሰጡት መልስ "አዎ" ብለዋል። ጨምረውም "ስድስት ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብን ለማስራብ ሙከራ ብቻ ሳይሆን፣ ምን እየተከሰተ እንደሆነ እንዳይታወቅም ጥረት እየተደረገ ነው" ብለዋል።

ትግራይ ውስጥ ሰዎች ስለመራባቸው የሚያጠያይቅ አይደለም። ነገር ግን በእንዲህ ያለው ሁኔታ መመዘኛ የሆኑት የምግብ አቅርቦትና የሞት መጠንን በሚመለከት የተደረገ ቅኝት ባለመኖሩ የመንግሥታቱ ድርጅት ችግሩን ረሃብ ለማለት እያቅማማ ነው።

የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ባለፈው ሰኔ ወር በቡድን 7 ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት በትግራይ ያለውን ሁኔታ ረሃብ ብሎ ለመጥራት "መቃብሮችን እስክንቆጥር ድረስ መጠበቅ የለብንም" ሲሉ አስቸኳይ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ገልጸው ነበር።

ጥያቄው ትግራይ ውስጥ ረሃብ መኖሩ ሳይሆን፣ ቸግሩ ከመቀረፉ በፊት ምን ያህል ሰዎች በረሃብ ምክንያት ሊሞቱ ይችላሉ? የሚለው ነው።

Short presentational grey line

*አሌክስ ደ ዋል ተፍትስ ዩኒቨርስቲ ፍሌቸር የግ እና ዲፕሎማሲ ትምህርት ቤትለም ሰላም ፋውንዴሽን ዋና ዳይሬክተር ናቸው።