በጊኒ መፈንቅለ መንግሥት የመሩት ኮሎኔል ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሐላ ፈጸሙ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ከአንድ ወር በፊት መፈንቅለ መንግሥት አካሂደው ወደ ሥልጣን የወጡት ኮሎኔል ማማዲ ዱምቡያ የጊኒ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሐላ ፈጸሙ።
በዚህም ባለፈው ዓመት በተካሄደ በወታደራዊ የመንግሥት ግልበጣ ሥልጣን የተቆጣጠሩት የ38 ዓመቱ የማሊው አሲሚ ጎይታን በመከተል የ41 ዓመቱ ወታደራዊ መኮንን ዱምቡያ በአፍሪካ ሁለተኛው ወጣት መሪ ለመሆን በቅተዋል።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ 30 በተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ወደ ሥልጣን የመጡት ኮሎኔሉ ማማዲ ዱምቡያ ከፍተኛ ተቃውሞና ውግዘት ግጥሟቸው ነበር።
የምዕራብ አፍሪካ አገራት አካባቢያዊ ድርጅት የሆነው ኤኮዋስና የአፍሪካ ሕብረት በመንግሥት ግልበጣው ሰበብ ጊኒን ከአባልነት አግደዋታል።
በተጨማሪም ኤኮዋስ መፈንቅለ መንግሥቱን በመሩት ወታደሮች ላይ ማዕቀብ የጣለ ሲሆን አገሪቱ በስድስት ወራት ውስጥ ወደ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንደትመለስም አሳስቧል።
የጊኒ ወታደራዊ መሪዎች አገሪቱን በሲቪል ወደሚመራ አስተዳደር ለመመለስ ዕቅዳቸውን ቢያሳውቁም የሽግግር ጊዜው ምንያህል ጊዜ እንደሚወስድ ግን በግልጽ ያስቀመጡት ነገር የለም።
ከአንድ ወር በፊት በተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት የ83 ዓመቱን አልፋ ኮንዴን ከሥልጣን ያስወገዱት ኮሎኔል ዱምቡያ እንዳሉት፤ እርምጃውን የወሰዱት በአገሪቱ በተንሰራፋው ሙስና፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እና የምጣኔ ሀብት ውድቅት ምክንያት ነው ብለዋል።
የወታደራዊው መፈንቅለ መንግሥቱ መሪዎች ከሥልጣናቸው ያነሷቸውን ፕሬዝዳንት ኮንዴን በቁጥጥር ስር አድርገዋቸው የሚገኙ ሲሆን "ደኅንነታቸው በተጠበቀ ቦታ" እንደሚገኙ ኮሎኔል ዱምቡያ ለፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
ነገር ግን የቀድሞው ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ አስካሁን የት እንደሚገኙ በግልጽ የታወቀ ነገር የለም።
በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ከመያዛቸው በፊት ብዙም የማይታወቁት ኮሎኔል ዱምቡያ፣ ከባልደረቦቻቸው ጎልተው እንዲወጡ ያደረጋቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ወታደራዊ ልምድ እንደሆነ የምዕራብ አፍሪካ አገራት የፖለቲካ ተንታኙ ፖል ሜሊ ይናገራሉ።
ኮሎኔል ማማዲ ዱምቡያ ፈረንሳይ ውስጥ ወታደራዊ ስልጠና አግኝተው በፈረንሳይ ጦር ሠራዊት ውስጥ ማገልገላቸው ይነገራል።
ኮሎኔሉ ለ15 ዓመታት በቆዩበት ወታደራዊ ሙያ ውስጥ በአፍጋኒስታን፣ በአይቮሪኮስት፣ በጂቡቲ፣ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እንዲሁም በተለየ ምደባ በእስራኤል፣ በቆጵሮስ፣ በዩናይትድ ኪንግደምና በጊኒ ውስጥ አገልግለዋል።
የጊኒው ፕሬዝዳንት ዱምቡያ እና ከእሳቸው ቀደም ብለው በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ሥልጣን የወጡት የማሊው ፕሬዝዳንት አሲሚ ጎይታ ጓደኛሞች እንደሆኑ አንድ የዜና ድረ ገጽ ዘግቧል።














