የጊኒ መፈንቅለ መንግሥት መሪዎች በሳምንታት ውስጥ አዲስ መንግስት ሊመሰርቱ ነው

አልፋ ኮንዴ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የጊኒውን ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴን ከስልጣን ያስወገደው የመፈንቅለ መንግስት መሪ በሳምንታት ውስጥ አዲስ "የህብረት" መንግስት እንደሚቋቋም ተናግረዋል።

ኮሎኔል ማማዲ ዱምቡያ በኮንዴ መንግስት ውስጥ ላገለገሉ ሚኒስትሮች እንደተናገሩት የቀድሞ ባለስልጣናትን ማደን አይኖርም።

ፕሬዝዳንት ኮንዴ በቁጥጥር ስር ሲሆኑ መጪው ዕጣ ፈንታቸው ግልፅ አይደለም።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት እና ኢኮዋስ መፈንቅለ መንግስቱን አውግዘው ስልጣኑ ወደ ሲቪል አመራር እንዲመለስ ጠይቀዋል።

"ማንኛውንም በጠመንጃ ኃይል የሚደረግ ስልጣን በጥብቅ አውግዛለሁ። ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጥሪ አቀርባለሁ" ብለዋል የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በትዊተር ገጻቸው።

የሠራዊቱን ልዩ ኃይል የሚመሩት ኮሎኔል ዱምቡያ አዲሱ መንግሥት መቼ እንደሚቋቋም አልተናገሩም።

በመግለጫቸውም "የሽግግሩን ሂደት ለማስቀመጥ ምክክር ይጀመራል። ከዚያም ሽግግሩን የሚመራ የብሔራዊ ህብረት መንግሥት ይቋቋማል" ብለዋል።

ለቀድሞው ሚኒስትሮች ከሃገር መውጣት እንደማይችሉ እና ተሽከርካሪዎቻቸውን ለወታደሩ ማስረከብ እንዳለባቸው ነግረዋቸዋል። የመሬት እና የአየር ድንበሮች እንደገና መከፈታቸውንም አስታውቋል።

ከስብሰባው በኋላ ኮሎኔል ዱምቡያ እሑድ በፕሬዚዳንቱ ሕንጻ አቅራቢያ ለበርካታ ሰዓታት ከባድ የተኩስ ልውውጥ መድረጉን ተከትሎ ውጥረት የነገሰበትን ዋና ከተማዋ ኮናክሪን ዞረው ተመልክተዋል።

በከተማዋ የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ እንደገለጸው ብዙዎች የወታደራዊ መሪውን ስም ሲጠሩ ነበር።

"በጣም ተደስተው ነበር። አንዳንድ ሰዎች ልብሳቸውን አውልቀው "ዱምቡያ ፣ዱምቡያ ፣ዱምቡያ "እና" ነፃነት፣ነፃነት፣ ነፃነት "ብለው ሲጮኹ ነበር ብሏል አልሀሰን ሲላህ ።

ፕሬዝዳንት ኮንዴ ከስልጣን መነሳታቸው እፎይታ ያገኙትን የብዙዎችን ስሜት ያንፀባርቃል ብሏል ዘጋቢው።

የማዕድን ኩባንያዎች ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ኮሎኔል ዱምቡያ አሳስበው በሃገር አቀፍ ደረጃ ከተጣለው የሰዓት እላፊ ነጻ ይሆናሉ ብለዋል።

ጊኒ በዓለም ላይ ትልቁ የአሉሚኒየም አካል የሆነው የባክሳይት አቅራቢ ናት። መፈንቅለ መንግሥቱን ተከትሎ አቅርቦት ላይ ስጋት በመኖሩ የአሉሚኒየም ዋጋ ከአሥር ዓመት ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል።

መፈንቅለ መንግስቱ እንዴት ተከናወነ?

እሑድ ምሽት በመንግስታዊው ቴሌቪዥን ላይ አንድ የወታደሮች ቡድን የክልል ገዥዎች በወታደራዊ አዛዦች ተተክተዋል፤ የተባረሩት የ 83 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ደህና ናቸው ግን በእስር ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

ኮሎኔልል ዱምቡያ እንዳሉት ወታደሮቻቸው ስልጣኑን የተቆጣጠሩት የተንሰራፋውን ሙስና፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና የመልካም አስተዳደር እጦትን ለማስቀረት ስለፈለጉ ነው።

ባለፈው ዓመት ፕሬዝዳንት ኮንዴ ለሦስተኛ የሥልጣን ዘመን ቢመረጡም አመጽ የቀሰቀሰ ተቃውሞ ተፈጥሮ ነበር።

አንጋፋው የተቃዋሚ መሪ በሀገሪቱ የመጀመሪያ ዲሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር እአአ በ 2010 ለመጀመሪያ ጊዜ ተመርጠዋል።

ምንም እንኳን አንዳንድ የኢኮኖሚ ዕድገትን ቢያስመዘግቡም ከዚያ በኋላ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና ተቺዎቹን በማንገላታት ተከሰዋል።

የተቃዋሚው ኤፍኤንዲሲ (ናሽናል ፍሮንት ፎር ዲፌንስ ኦፍ ዘ ኮንስቲትዩሽን) መስራች አባል ማሞዱ ናግሌን ባሪ ለቢቢሲ ስለ መፈንቅለ መንግሥቱ የተደባለቀ ስሜት ቢኖራቸውም በአብዛኛው እንደሚቀበሉት ተናግረዋል።

"በተፈጠረው ነገር እያዘንኩ እደሰታለሁ" ብለዋል።

"በመፈንቅለ መንግሥት መደሰት አንፈልግም። ሆኖም እንደ ጊኒ ባሉ እንደ አንዳንድ ሁኔታዎች በሚሆነው ነገር ደስተኞች ነን እንላለን። ምክንያቱም ያለበለዚያ ሃገሪቱ ለዘላለም ስልጣን ላይ ለመቆየት በሚፈልግ የአንድ ሰው ማለቂያ የሌለው ኃይል ውስጥ ተጣብቃለች" ብለዋል።

ባሪ አክለውም ወታደሮቹ ስልጣኑን ለሲቪሎች እንደሚሰጡ ተስፋ አድርገዋል።

የጊኒ መፈንቅለ መንግሥት እአአ ከነሐሴ 2020 ጀምሮ በክልሉ ዴሞክራሲን ለማዳከም ሙከራ ሲደረግ ለአራተኛ ጊዜ ነው። በማሊ ሁለት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስቶች እና በኒጀር ያልተሳካ ሙከራ ተደርጓል።