በመቶዎች የሚቆጠሩ የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ከትግራይ ለምን ሳይወጡ ቀሩ?

የፎቶው ባለመብት, UN
- ፀሐፊ, ፒተር ምዋይ
- የሥራ ድርሻ, ቢቢሲ ሪያሊቱ ቼክ
በትግራይ ያለው የእርዳታ ምግብ አቅርቦት ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ በሚነገርበት በአሁኑ ጊዜ፤ አስፈላጊውን እርዳታ ለማድረስ ወደ ክልሉ የገቡ የጭነት ተሽከርካሪዎች መንቀሳቀስ ያልቻሉበትን ሁኔታ በተመለከተ የሚቃረኑ መረጃዎች እየወጡ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ከሐምሌ መጀመሪያ እስከ መስከረም መጀመሪያ ድረስ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተነስተው በመቶዎች የሚቆጠሩ እርዳታ ጫኝ ከባድ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ቢሄዱም አልተመለሱም።
ተሽከርካሪዎቹ ምን አጋጠማቸው?
ወደ ትግራይ የእርዳታ አቅርቦት ለማድረስ ያለው ዋነኛው አማራጭ በአፋር በኩል የሚደረግ የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት ነው።
በተባበሩት መንግሥታት ተቋማት ግምት መሠረት አስፈላጊውን እርዳታ ለማድረስ ምግብ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶችና ነዳጅ የጫኑ 100 ተሽከርካሪዎች በየቀኑ ወደ ክልሉ መግባት ይኖርባቸዋል።
እስከ መስከረም 06/2014 ዓ.ም ባሉት ሁለት ወራት ውስጥ 466 ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች በአፋር በኩል ወደ ትግራይ ቢገቡም ከመካከላቸው 38ቱ ብቻ ናቸው የተመለሱት ብሏል የተባበሩት መንግሥታት።
"ይህ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትን ወደ ትግራይ ለማድረስ በአሁኑ ጊዜ ቀዳሚው እንቅፋት ነው። ባለው የጭነት ተሽከርካሪዎች እጥረት ምክንያት ከፍተኛ መጠን ያላቸው መኪኖችን ማሰባሰብ አልቻልንም" ሲሉ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
ለምን ተሽከርካሪዎቹ ከትግራይ አልተመለሱም?
ቢቢሲ የተባበሩት መንግሥታትን የጭነት ተሽከርካሪዎቹ የት እንዳሉ ቢጠይቅም እስካሁን ዝርዝር ማብራሪያ ለመስጠት ሳይችል ቀርቷል።
ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ጦርነት ውስጥ የሚገኙት የትግራይ ኃይሎች ግን ለዚህ መንግሥትን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
"የጭነት ተሽከርካሪዎቹ ሹፌሮች የተሰጣቸው የነዳጅ መጠን ትግራይ ድረስ ለሚጓዙበት የአንድ መስመር ጉዞ የሚበቃ ብቻ ነው። ለእንደዚህ አይነት ስምሪት እንደሚደረገው ለመልስ ጉዞ የሚሆን የመጠባበቂያ ነዳጅ አልተሰጣቸውም" ሲል ህወሓት ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።
ጨምሮም አብዛኞቹ የትግራይ ተወላጅ የሆኑት የተሽከርካሪዎቹ ሹፌሮች ከትግራይ ክልል ውጪ በሚገኙ የፍተሻ ኬላዎች ላይ ባሉ የፌደራሉ ሠራዊት አባላትና በአካባቢዎቹ የደኅንነት ባለሥልጣናት ጥቃትና ማስፈራራት ይደርስባቸዋል ብሏል።
በዚህም ምክንያት በመልስ ጉዟቸው በእንዲህ ያለ ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ማለፍ ስለማይፈልጉ ለመመለስ ፈቃደኛ አይደሉም ሲል ገልጿል።
ወደ ክልሉ ተይዞ በሚገባው የገንዘብ መጠን ላይ ቁጥጥር ስለሚደረግና በትግራይ ውስጥ የባንክ አገልግሎት ስለተቋረጠ እዚያ ሲደርሱ የሚፈልጉትን ያህል ገንዘብ ሊያገኙ አይችሉም ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የእርዳታ ምግብ ጭነው ወደ ተግራይ የገቡ ተሽከርካሪዎች አለመመለስ በእርዳታው አቅርቦት ላይ እንቅፋት መፍጠሩን ገልጿል።
ነገር ግን የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ተሽከርካሪዎቹ ከክልሉ እንዳይወጡ አድርጓል የሚለውን ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአደጋ ስጋት አስተዳደር ኮሚሽነር የሆኑት አቶ ምትኩ ካሳ አይቀበሉትም።
የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደሚሉት የእርዳታ ምግብ ይዘው ወደ ትግራይ ክልል የገቡት ከባድ ተሽከርካሪዎች በህወሓት ቁጥጥር ስር ገብተው ሊሆን ይችላል ይላሉ፤ ነገር ግን ይህንን የሚያረጋግጥ ማስረጃ የለም።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ስለ ነዳጅ ሁኔታስ ምን እናውቃለን?
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) አሽከርካሪዎቹ ላለመመለሳቸው ያቀረቡት ምክንያት የነዳጅ እጥረት በመኖሩ እንዲሁም ለደኅንነታቸው በመስጋታቸው ነው ብሏል።
የተባባሩት መንግሥታት ለተወሰኑ ሳምንታት በትግራይ ስላለው የነዳጅ አቅርቦት ያለውን ስጋት የገለጸ ሲሆን ቀደም ብሎም የነዳጅ ቦቴዎች ወደ ክልሉ እንዳይገቡ በመከልከሉ ቅሬታ ሲያሰማ ቆይቷል።
የተባበሩት መንግሥታት በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ "የነዳጅ ቦቴዎችን ወደ ትግራይ ለማስገባት የተጠየቀው ፈቃድ በአፋር ክልል ባለሥልጣናት ተከልክሏል" ብሏል።
ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ በተደረገው የተባበሩት መንግሥታትና የእርዳታ ድርጅቶች ስብሰባ ላይም በክልሉ የጥሬ ገንዘብ እና የነዳጅ እጥረት ተሽከርካሪዎቹ እንዳይመለሱ ካደረጋቸው ተግዳሮቶች መካከል መሆናቸው ተጠቅሷል። ድርጅቶቹ ተሽከርካሪዎቹ እንዲይዙ የተፈቀደላቸው የነዳጅ መጠን ቦታው ድረስ የሚያደርሳቸውን ያህል ብቻ እንደነበር አስታውሰዋል።
ድርጅቶቹ እንዳሉት የጥሬ ገንዘብ እጥረትና ነዳጅ ማግኘት አለመቻል ተደማምሮ ተሽከርካሪዎቹ ከትግራይ መዲና መቀለ ለመመለስ ፈተና ሆኖባቸዋል።
የተባበሩት መንግሥታት በትግራይ በሳምንት 200 ሺህ ሊትር ነዳጅ እንደሚያስፈልግ ገልጾ፤ ከፈርንጆቹ ሐምሌ 12 ጀምሮ ግን ትግራይ የደረሰው ነዳጅ 300 ሺህ ሊትር ብቻ ነው ብሏል።
የመጨረሻው የነዳጅ ቦቴ ትግራይ የደረሰው ሐምሌ 29 ቀን መሆኑን የጠቀሰው ድርጅቱ የነበረው የነዳጅ ክምችት መስከረም ከሁለት ሳምንት በፊት አልቋል ብሏል።
ድርጅቱ አክሎም ከመስከረም 21 ጀምሮ ዘጠኝ የነዳጅ ቦቴዎች በአፋር ክልል መዲና ሰመራ ቆመው ወደ ትግራይ ለመጓዝ ከመንግሥት ፈቃድ እየተጠባበቁ መሆናቸውን ገልጿል።
የጸጥታ ሁኔታው ምን ይመስላል?
በቅርቡ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች ከክልሉ ውጪ ባሉ የፍተሻ ጣቢያዎች የተለያዩ ጥቃቶች እንደደረሱባቸው በትግራይ የሚገኙ የሰብዓዊ እርዳታ ባለሥልጣናት ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት በአሽከርካሪዎቹ ከተጠቀሱት ምክንያቶች መካከል ከሰመራ ወደ መቀለ በሚወስደው መንገድ ላይ ለድብደባ፣ ትንኮሳ፣ ማስፈራሪያና እና ዘረፋ ስለደረሰባቸው ለደኅንነታቸው መስጋታቸው ነው ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ነሐሴ ወር ላይ በትግራይ ላለው ተልዕኮ የመንገድ ትራንስፖርት ሁኔታ በሚገመግምበት ወቅት በአፋር ክልል የታጠቁ ፖሊሶች ተፈጽሟል የተባለ የማዋከብ እና የመብት ጥሰት መፈፀሙን ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽ ለማድረግ ወደ ትግራይ በሚወስዱት መንገዶች ላይ ይገኙ የነበሩ ሰባት የፍተሻ ጣቢያዎችን ወደ ሁለት መቀነሱን ገልጿል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ቢልለኔ ስዩም እንዳሉት "ምንም እንኳን የሰብአዊ እርዳታን በተቀላጠፈ መልኩ ለማጓጓዝ የፍተሻ ጣቢያዎች እንዲቀነሱ ቢደረግም በሰብአዊ ድርጅቶች የሚላኩ እርዳታ ጫኑ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ግን አልጨመረም" ብለዋል።












