የእንግሊዙ ግዙፍ ሲጋራ አምራች ኩባንያ ለሙጋቤ ፓርቲ ጉቦ ለመስጠት ተደራድሮ ነበር ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቢቢሲ ፓኖራማ የምርመራ ዘገባ የእንግሊዙ ግዙፉ ሲጋራ አምራች ኩባንያ ለቀድሞ የዚምባብዌ መሪ ፕሬዝደንት ሮበት ሙጋቤ ፓርቲ ጉቦ ለመክፈል ተደራድሮ እንደነበረ አረጋገጠ።
ብሪቲሽ አሜሪካን ቶባኮ የተሰኘው ኩባንያ እአአ 2013 ላይ ለፕሬዝደንት ሮበርት ሙጋቤ ፓርቲ ዛኑ-ፒኤፍ ፓርቲ ከ300ሺህ-500ሺህ የአሜሪካ ዶላር ለመክፈል መደራደሩን መረጃዎች አሳይተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ኩባንያው በደቡብ አፍሪካ ጉቦ መክፈሉ እና ተቀናቃኞቹን ለመጉዳት ሕገ-ወጥ በመሆነ መንገድ ክትትል አድርጓል። ኩባንያው በደቡብ አፍሪካ ወደ 200 ለሚጠጉ ሚስጥራዊ መረጃ አቀባዮቹ ገንዘብ ሲከፍልም ነበር።

ኩባንያው አብዛኛውን የደህንነት ሥራዎች እንዲሰራለት የደቡብ አፍሪካ የግል ኩባንያ ለሆነ ፎረንሲክ ሴኪዩሪቲ ሰርቪስ (ኤፍኤስኤስ) ውል ሰጥቷል።
በአንድ ሰነድ ላይ ይህ ኤፍኤስኤስ የተባለው ኩባንያ የብሪቲሽ አሜሪካን ቶባኮ ተወዳዳሪ የሆኑ በዚምባብዌ የሚገኙ ሦስት ኩባንያዎች እንዲዘጉ ትዕዛዝ ተሰጥቶት ነበር።
ይህንም ለመፈጸም ኤፍኤስኤስ በተቀናቃኝ ኩባንያዎች ላይ መረጃ ለመሰብሰበ ለተቋማት ክፍያ ፈጽሟል። ይህ የኤፍኤስኤስ ተግባር ሲጋለጥ ሦስት ዳይሬክተሮቹ በቁጥጥር ሥር ውለው ነበር። ይህን ተከትሎም ፕሬዝደንት ሙጋቤ የኤፍኤስኤስ ተግባር እና የብሪቲሽ አሜሪካን ቶባኮ ተሳትፎን በማብጠልጠል ንግግር አድርገዋል።
ይሁን እንጂ የፓናሮማ የምርመራ ዘገባ እንዳረጋገጠው፤ በቁጥጥር ሥር በዋሉት ግለሰቦች ጉዳይ ተገናኝቶ ውይይት ለማድረግ ብሪቲሽ አሜሪካን ቶባኮ ለዚምባብዌ ባለስልጣናት ጉቦ ለመክፈል ተደራድሮ ነበር።

ብሪቲሽ አሜሪካን ቶባኮ ማነው?
- ብሪቲሽ አሜሪካን ቶባኮ ከዓለማችን ግዙፍ ሲጋራ አምራች ኩባንያዎች መካከል አንዱ ነው።
- በዩናይትድ ኪንግደም ከሚገኙ ግዙፍ 10 ኩባንያዎች አንዱ ነው።
- ባለፈው ዓመት 650 ቢሊዮን ሲጋራዎችን ሸጧል።

የዚምባብዌ ባለስልጣናት ኩባንያው ገዢው ፓርቲ ላለበት ምርጫ የገንዘብ ድጋፍ ቢያደር ከፕሬዝደንቱ ጋር ሊገናኝ እንደሚችል እና ግለሰቦቹን የተመለከተው ችግር መፍትሄ ያገኛል ስለማለታቸው በምርመራ ዘገባው ተመልክቷል።
ኩባንያው ከ300ሺህ-500ሺህ የአሜሪካ ዶላር እንዲከፍል ቢጠየቅም ኩባንያው የተጠየቀውን ገንዘብ ስለመክፈሉ የተረጋገጠ ነገር የለም። ይሁን እንጂ በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩት ግለሰቦች በቀናት ልዩነት ከእስር ወጥተዋል።
ብሪቲሽ አሜሪካን ቶባኮ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
ከዚህ በተጨማሪ ለብሪቲሽ አሜሪካን ቶባኮ የደህንነት ሥራዎችን ሲሰራ የነበረው ፎረንሲክ ሴኪዩሪቲ ሰርቪስ (ኤፍኤስኤስ) ሌሎች ሲጋራ አምራች ኩባንያ ተቀናቃኝ ኩባንያዎች ላይ ለመሰለል የፖሊስ ካሜራ ኔትዎርክ ተጠቅሟል። የፖሊስ ካሜራ ለመጠቀምም ለፖሊስ እና የጉምሩክ ኃላፊዎች ጉቦ ከፍሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ኤፍኤስኤስ የተባለው ኩባንያ የተቀናቃኝ መስሪያ ቤት ሰራተኞችን ስልክ ጠልፏል፣ የተቀናቃኝ ኩባንያ ሠራተኞች መረጃ እንዲሰጡት በገንዘብ ደልሏል ተብሏል።












