ህወሓት የአፍሪካ ሕብረትን በወገንተኝነት ከሰሰ

የአፍሪካ ሕብረት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአፍሪካ ሕብርት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ መሾሙን ተከትሎ ህወሓት ሕብረቱን በወገንተኝነት ከሰሰ።

በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆም ድርድር እንዲደረግና ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈለግ የተለያዩ ወገኖች ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ።

ትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ላለፉት አስር ወራት ሲካሄድ የቆየው ጦርነት ከሰኔ ወር ማብቂያ ወዲህ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ተስፋፍቷል።

ባለፈው ሳምንት አህጉራዊው ድርጅት የአፍሪካ ሕብረት ለጦርነቱ መፍትሔ ለመፈለግ እንዲራዳው የቀድሞውን የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሌሴጉን ኦባሳንጆን የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ሆነው በሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ተሹመዋል።

ነገር ግን ይህን በቀጠናው ሰላም፣ ደኅንነትና መረጋጋት እንዲሰፍን እንዲሁም የፖለቲካ ውይይትን ለማበረታታት የሚያደርገው ጥረት ያግዛል ተባለው የአፍሪካ ሕብረት ሹመትን ተከትሎ በሕብረቱ አቋም ላይ ከህወሓት በኩል ጥያቄን አስከትሏል።

ሕብረቱ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆን እንደ አሸማጋይ መሾሙን ካሳወቀ ከቀናት በኋላ አማጺው ቡድን የአፍሪካ ሕብረትን በወገንተኝነት በመክሰስ ጥያቄ አንስቷል።

የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ የአፍሪካ ሕብረት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር መወገኑን በመግለጽ ባለፉት አሰር ወራት የቆየውን ግጭት ተገቢውን ትኩረት አልሰጠውም ሲሉ ከሰዋል።

አቶ ጌታቸው በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ላይ እንዳሰፈሩት ህወሓት አሸማጋይ መሰየሙን እንደማይቃወም አመልክተው ነገር ግን ይህ ተልዕኮ ይሳካል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሽብርተኛ ድርጅት ብሎ ከሰየመው ከህወሓት ጋር ምንም አይነት ድርድር እንደማይኖር ማሳወቁ ይታወሳል።

ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወራትን ያስቆጠረው ጦርነት በሰኔ ወር ማብቂያ ገደማ የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከክልሉ ካስወጣ በኋላም ቀጥሎ ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳትን እያስከተለ ይገኛል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮቹን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱን ተከትሎ የህወሓት ኃይሎች በአጎራባቾቹ የአማራና የአፋር ክልሎች ውስጥ በመግባት ጥቃት በመፈጸማቸው የተነሳ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንደተፈናቀሉ ተዘግቧል።

በአሁኑ ወቅትም በአማራና በአፋር ክልል ውስጥ የፌደራል መንግሥት ከክልል ኃይሎች ጋር በመሆን ከህወሓት አማጺያን ጋር ጦርነት እያካሄዱ ስለመሆኑ ተዘግቧል።

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በተወያየበት ጊዜ ዋና ጸሐፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሁሉም አካላት ተኩስ አቁመው ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈልጉ ጥሪ አቅርበዋል።

"ሁሉም ወገን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁሞ ወደ ድርድር መምጣት አለበት። ስለኢትዮጵያ ሲሉ ሰላማዊ መንገድን አማራጭ ማድረግ አለባቸው። ሁሉን አካታች የፖለቲካ ውይይት ያስፈልጋል። የውጭ ኃይሎችም ከአገሪቱ መውጣት አለባቸው" ብለው ነበር።

በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ለፀጥታው ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር "የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላም ለማስፈን የወሰነውን የተናጠል ተኩስ አቁም ህወሓት እንዲቀበል ጫና መረደግ አለበት" ሲሉ መጠየቃቸው ይታወሳል።

ከሳምንት በፊት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍፊ ፌልትማን ወደኢትዮጵያና ሌሎች የአካባቢው አገራት በመምጣት ከከፍተኛ ባለሥልጣንት ጋር መወያየታቸው የተነገረ ሲሆን ስለጉብኝታቸው በይፋ የተሰጠ መግለጫ የለም።

በአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ሆነው ተሰየሙት ኦባሳንጆ ቀዳሚ ሥራ ለወራት የዘለቀውና በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበሩ ሙሳ ፋኪ ማህማት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ፤ የአፍሪካ ሕብረትን የጋራ ጥቅም ለማስከበር ይህንን ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ኃላፊነት በመቀበላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።