ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ ያላቸው ተሳትፎ
ለአስር ዓመታት ያህል በአሜሪካ የኖረችው ጄነት ለማ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰችው ከአምስት ዓመት በፊት በ2016 (እኤአ) ነው።
ወደ አገሯ ከመጣች በኋላም ጋበር ዌር (Gaber Wear) የተሰኘ አልባሳት የሚያመርት ድርጅት በመክፈት ወደ ሥራ ተመሳርታለች።
በአሜሪካ ጥሩ ገቢ የምታገኝበት ሥራ እንደነበራት የምትናገረው ጄነት፣ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የተሻለ እና ለራሷም ሆነ ለሌሎች የሥራ ዕድል የምትፈጥርበት ሥራ ላይ መሰማራት ለረዥም ጊዜ ስትፈልግ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግራለች።
ከልጅነቷ ጀምሮ በፋሽን ዙሪያ የተለየ ፍላጎት እንደነበራት የምታስረዳው ጄነት በዓለም አቀፍ ገበያ ተፎካካሪ የራሷ የሆነ ብራንድ ምርት እንዲኖራት ትፈልግ እንደነበር ታስረዳለች።
"የምሰማራበት ሥራ ማኅበራዊ አስተዋጽኦ ያለው ቢሆን እመርጥ ነበር" የምትለው ጄነት፣ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ይህ መሰረታዊ ምክንያት እንደሆናት ገልጻለች።
በአሁኑ ወቅት በጋበር ዌር በቋሚና በጊዜያዊነት 100 ያህል ሠራተኞች ተቀጥረው በሥራ ላይ ናቸው።
ጄነት የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ የራሷን አስተዋጽኦ ማበርከቷን በመግለጽ፣ ምርቷንም ወደ አሜሪካ እና ካናዳ መላክ መጀመሯን ታስረዳለች።
የኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ቢዝነሶች
እኤአ በ2020 ከአገር ውጪ በተለያዩ የዓለም ክፍል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ እና ለተለያዩ ቢዝነሶች ማስኬጃ 3.7 ቢሊዮን ዶላር ወደ አገር ቤት መላካቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
ከባሕር ማዶ ወደ አገር ውስጥ የሚላከው ገንዘብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሲሆን በአንጻሩ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች የሚያንቀሳቅሷቸው ቢዝነሶችም ከፍ እያሉ መምጣታቸውን መንግሥት ይገልጻል።
ዲያስፖራዎች የሥራ ፈቃድ የወሰዱባቸው ቢዝነሶች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት ከፍ እያለ መምጣቱን ከዳያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እንድሪስ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በርካታ ያሥራ ዘርፎችን ባስተጓጎለበት ባለፈው ዓመት ብቻ 35 ፈቃዶችን ለዲያስፖራዎች መሰጠቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከሦስት ዓመት በፊት 54 በዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ተከፍተው ወደ ሥራ የገቡ ቢዝነሶች እንደነበሩ አመልክተው በዚህ ዓመት ደግሞ 84 ዲያስፖራዎች በተለያዩ ዘርፎች ለመሰማራት ፈቃድ መውሰዳቸውን ይገልጻሉ።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ 5100 ኢንቨስትመንቶች በዲያስፖራው ስም ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ምክትል ዳይሬክተሩ ይናገራሉ።
ከዚህ የዲያስፖራ ኢንቨስትመንት ውስጥ ደግሞ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ 40 በመቶ ያህሉን እንደሚሸፍን አክለዋል።
በመቀጠልም ሪል ስቴት፣ ማሽነሪ፣ የኪራይ አገልግሎት፣ የግብርና እንዲሁም አገልግሎት ዘርፎቸ ዲያስፖራዎች በቅደም ተከተል የተሰማሩባቸው ዘርፎች ናቸው።
መንግሥት ዲያስፖራው በተለያዩ ዘርፎች እንዲሰማራ ለማድረግ ሁለት አማራጮችን እንደሚጠቀም አቶ መሐመድ ለቢቢሲ ያስረዳሉ።
የመጀመሪያው በአገሪቱ ውስጥ ሕጋዊ፣ ተቋማዊ ጉዳዮች ለዲያስፖራ ኢንቨስተሮች ምቹ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። ሌላው ደግሞ ዲያስፖራው ወደ አገሩ መጥቶ ሀብቱን እንዲያፈስ ማንቀሳቀስ፣ ማበረታታት እንዲሁም መደገፍ ናቸው።
እንደ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እንድሪስ ከሆነ፣ ከ84 በላይ የሚሆኑ የዲያስፖራ ኢንቨስትመንቶች ብቻ ከ4 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል በማፍሰስ ለበርካታ ዜጎች ሥራ መፍጠራቸውን እንደማሳያ በማንሳት ኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ በሥራ ፈጠራ ረገድ ያላቸወን አስተዋጽኦ ያብራራሉ።
በአጠቃላይ 30 ሺህ ያህል የሥራ እድሎች በዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ኢንቨስትመንቶች ብቻ በተከፈቱ ዘርፎች ላይ መፈጠራቸውንም ይጠቅሳሉ።
በአሁን ጊዜ ከመንግሥት ቀጥሎ ትልቁ ቀጣሪ የዲያስፖራ ኢንቨስትመንት መሆኑንም አቶ መሐመድ ይጠቅሳሉ።
ዲያስፖራውን የሚስቡ የኢንቨስትመንት መስኮች
የተባበሩት መንግሥታት ከንግድ እና እድገትጋር ተያይዞ ባወጣው መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ ረገድ ከአህጉሪቱ አምስት አገራት መካከል አንዷ መሆኗን ያስቀምጣል።
በ2019 (እአአ) ብቻ ኢትዮጵያ ቀጥተኛ የሆነ ውጪ ኢንቨስትመንት በመሳብ 2.5 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች።
ከውጭ አገር በመምጣት በተለያዩ የኢንቨስትመንትዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙት አቶ አዲስ ዓለማየሁ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እና ዲያስፖራ ኢንቨስተሮች ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳላቸው ያብራራሉ።
ከሁለት ዓመታት በፊት ወደ አገሪቱ የመጡት ከፍተኛ የቢራ አምራች ኩባንያዎችን በማንሳት ዲያስፖራው አገሩ በመምጣት ኢንቨስት እንዲያደርግ በማነሳሳት ረገድ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ያስረዳሉ።
ዲያስፖራዎች በኢትዮጵያ የትኛውም ዘርፍ መጥተው ቢሰማሩ ያለው ዕድል እጅግ በጣም ሰፊ መሆኑን በማስረዳት፣ በይበልጥ ደግሞ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ)፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ ግብርና፣ ሎጀስቲክስ ዘርፎች ከፍተኛ የመሳብ አቅም እንዳላቸው ያብራራሉ።
ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት ለማድረግ የሚያስቡ ዲያስፖራዎች በቅድሚያ ምን ማወቅ አለባቸው ተብለው የተጠየቁት አቶ አዲስ አለማየሁ "ትክክለኛ መረጃ ከትክክለኛው ሰው ማግኘት ቀዳሚው ነው" ሲሉ ያነሳሉ።
በርካታ ሰዎች ከጓደኞቻቸው እና ከጎረቤቶቻቸው ምክር በማግኘት ወደ ኢንቨስትመንት ገብተው ችግር ውስጥ እንደሚወድቁ ይናገራሉ።
ሌላው ግለሰቦች ያላቸውን ተፈጥሯዊ አቅም እና ክህሎት አልያም የሙያ ዳራ በማየት በዚያ ላይ ቢሰማሩ ሲሉ ይመክራሉ።
አቶ አዲስ በተጨማሪ የሚሰጡት ምክር ከማኅበረሰቡ ጋር ተከባብሮ እና ተነጋግሮ መስራትን ነው።
የአካባቢው ነዋሪዎች ስለ አካባቢያቸው በሚገባ እንደሚያውቁ እና ያለውን ሁኔታ እንደሚረዱ በመግለጽ ዲያስፖራው በውጪው ዓለም የቱንም ዓይነት ልምድ ቢኖረው እንኳን የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማክበር መንቀሳቀስ ለስኬት ወሳኝ መሆኑን ያነሳሉ።