የጥቁር ገበያው ምንዛሪ መናር በኢኮኖሚው ላይ ምን ጫና ይዞ ይመጣል?

በአዲስ አበባ መደበኛ ባልሆነው የውጭ ምንዛሬ መስመር በሕገወጥ መንዛሪዎች የሚመራው የጥቁር ገበያ ባለፉት ጥቂት ቀናት ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ አንድ ዶላር በጥቁር ገበያው ከ64 እስከ 68 ብር ድረስ በመመንዘር ላይ እንደሚገኝ እና በተለያዩ ሁኔታዎች ይህ ዋጋ እስከ 72 ብር ድረስ ከፍ እንደሚል በዚሁ ሥራ ላይ ያለ ግለሰብ ለቢቢሲ ተናግሯል።

በመደበኛው የምንዛሪ ገበያ አንድ ዶላር በ45 ብር እየተመነዘረ ይገኛል።

በአሁኑ ጊዜ በጥቁር እና መደበኛ ገበያው መካከል ያለው ልዩነት ከ20 ብር በላይ ሆኗል። ይህም ከዛሬ ሦስት ዓመት ሐምሌ 2010 ከነበረበት ጋር ሲነጻጸር የእጥፍ ልዩነት አለው። በወቅቱ አንድ ዶላር በጥቁር ገበያው በ31 ብር ይመነዘር ነበር።

በመደበኛ ገበያውም ላይም ቢሆን ቀላል የማይባል ከፍተኛ ማሻቀብ ታይቶበታል። ከሰባት ወራት በፊት ከ40 ብር ያልተሻገረው የመደበኛው ገበያ ምንዛሪ አሁን የአምስት ብር ጭማሪ አሳይቷል። እንዲሁም በ13 ዓመታት ውስጥ የአምስት እጥፍ ጭማሪ ታይቷል።

"የጥቁር ገበያው ምንዛሪ መናር እየተባባሰ እንጂ እየተቃለለ ይሄዳል የሚል እምነት የለኝም" የሚሉት ለዓመታት የኢትዯጵያን የምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ሲተነትኑ የቆዩ ባለሞያ ናቸው።

በሥራቸው ጠባይ ምክኒያት ስማቸው እንዳይጠቀስ የመረጡት እኚሁ የምታኔ ሀብት ባለሞያ መንግሥት የብርን ምንዛሪ ለማዳከም የሚከተለውን ፖሊሲ ለክርክራቸው እንደማስረጃነት ያቀርባሉ።

"ይህ ሰዎች ቁጠባቸውን በዶላር እንዲያደርጉ ስለሚያበረታታ የጥቁር ገበያውን ዋጋ ይጨምረዋል። እንደተለመደው ወደ ውጪ ከምንልከው ከውጭ የምናስገባው ጋር ሲነጻጸር እጅግ ያነሰ ስለሆነ በአገሪቱ ያለው የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት እጅግ የተጋነነ ሆኖ ይቀጥላል" ሲሉ አክለዋል።

"ግጭቶች እና ተዛማጅ ብቅ ብቅ እያሉ ያሉ ፍላጎቶች የመንግሥትን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ይጨምሩታል። ይህ ማለት መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ከግሉ ዘርፍ ጋር ይወዳደራል ማለት ነው። ስለዚህ የግሉ ዘርፍ ብቸኛ አማራጩ ወደሆነው የትይዩ ገበያ ይሸጋገራል" ሲሉ የምጣኔ ሀብት ተንታኙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ኢኮኖሚው ላይ የሚጣሉ ማዕቀቦች መንግሥት ከውጭ አገራት በሚያገኛቸውን የምንዛሪ ፈሰሶች ላይ ጫና ይኖራቸዋል ያሉት ባለሙያው፤ ግጭቶች ሲኖሩ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እና ይዞት የሚመጣው ጥሬ ምንዛሬም አብሮ ቀሪ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

በባንክ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ትንታኔዎችን በመስጠት የሚታወቁት እና መቀመጫቸውን በእንግሊዝ ለንደን ያደረጉት አብዱልመናን መሐመድ በመደበኛ እና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው ልዩነት ለዓመታት በ20 እና 30 በመቶ መካከል መቆየቱን ያስታውሳሉ። አሁን ይህ ልዩነት ወደ 50 በመቶ አሻቅቧል ይላሉ።

የዚህ ቀጥተኛ ውጤትም አሁንም በከፍተኛ መጠን እየጨመረ በመጣው የዋጋ ግሽበት ላይ እንደሚበረታ አብዱልመናን ይናገራሉ።

ለዚህም ምክኒያቱ አስመጪዎች የውጭ ምንዛሪ ከባንኮች ስለማያገኙ ከዚሁ የጥቁር ገበያ በሚያገኙት ምንዛሪ እቃዎችን በማስመጣታቸው ነው ሲሉም ይከራከራሉ።

በተጨማሪም መንግሥት ይህንን በጥቁር እና በመደበኛው ገበያ መካከል ያለውን ልዩነት ለመሙላት ሲል በፍጥነት የብርን ዋጋ ማዳከሙ አይቀሬ ነው ሲሉ አብዱልመናን ለቢቢሲ ተናግረዋል። በተጨማሪም የኢኮኖሚው አይገመቴነት ባለሀብቶች ሀብታቸውን እንዳያፈሱ ያግዳል ብለዋል።

"የብር በፍጥነት ዋጋ ማጣት ከውጭ የሚገኙ ብድሮችን የመክፈል አቅምን ያዳክማል። ይህ የመንግሥትም ሆነ የግል ተበዳሪዎችን ኪሳራ ውስጥ ሊከት ይችላል። ብድሩንም ሆነ ወለዱን በውጭ ምንዛሪ የመቀየር ኃላፊነት የሚወድቅበት መንግሥትም ከፍተኛ ጫና ውስጥ ይወድቃልል" ሲሉም አክለዋል።

ትሬዲንግ ኢኮኖሚክስ ከተሰኘ ድረ-ገጽ የተገኘ መረጃ እንደሚያመላክተው ባለፉት 10 ዓመታት በባንኮች የዶላር ዋጋ በ28 ብር ገዳማ ጭምሯል። 2003 ዓ.ም. ላይ በባንክ 1 የአሜሪካ ዶላር በ16 የኢትዮጵያ ብር ይመነዘር ነበር።

ይህ አሳሳቢ ጉዞ ወዴት ያመራል ለሚለው ምላሽ የሰጡት የምጣኔ ሀብት ተንታኙ "ትንበያዎች የሚያሳዩት እኤአ 2022 መደበኛው ምንዛሪ ወደ 47̂ ነጥብ 7 ብር እንደሚያመራ ብሎም በ 2023 ወደ 54 ነጥብ 1 ብር ከፍ እንደሚል ነው። ቁጥሮቹን ብንተዋቸው እንኳን አሁን ያለው አካሄድ የሚያሳየን በእርግጠኝነት የብር ምንዛሪ እየተዳከመ እንደሚሄድ ነው" ሲሉ አስረድተዋል።

የኑሮ ውድነት፣ የአገር ውስጥ ኢኮኖሚው በዶላር መንቀሳቀስ (dollarization of domestic economy) እንዲሁም የድህነት መባባስ፣ የብር ዋጋ መውደቅ የአጭር ጊዜ ጫናዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተንታኙ ገልጸዋል። እንዲሁም ይህ በጊዜ ካልተገታ ወደ ሕዝባዊ አመጽ የሚያመራበት እድል እንዳለም አሳስበዋል።

በረጅም ጊዜ ኢኮኖሚው ሙሉ በሙሉ የመውደቅ ቀውስ (Full blown economic crisis) ሊጋረጥበት እንደሚችል ጠቅሰው ይህም ኢኮኖሚው ከተለያዩ አቅጣጫ ቀውሶች ሲገጥሙት የሚከሰት መሆኑን ያስረዳሉ።

"የውጭ ንግድ፣ የገንዘብ ፖሊሲው፣ ምርት፣ የብድር አስተዳደር ብሎም በኢንቨስትመንት ላይ የሚያሳድረው ጫና የኢኮኖሚ ውድቀት (Full blown economic crisis) ሊያጋጥም የሚችልበት እድል አለ" ሲሉም ገልጸዋል።

የባንክ ዘርፍና እና የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አብዱልመናን በበኩላቸው መንግሥት ይህንን ችግር ለመፍታት ወይም ለማቃለል የብርን በፍጥነት መዳከምን ጨምሮ በርካታ የአስተዳደር እርምጃዎችን መውሰድ አለበት ብለው ያምናሉ። በተጨማሪም ጥብቅ የሆነ የሞኒተሪ ፖሊሲን መተግበር ከመፍትሄዎቹ መካከል እንደሆኑም ገልጸዋል።