"ሚዲያው እየመጣ ላለው አዲስ አይነት ጥቃት መዘጋጀት አለበት" ፀዳለ ለማ

የፎቶው ባለመብት, CPJ
ከቀናት በፊት የምዝገባ ፈቃዱ ታግዶ የነበረው የአዲስ ስታንዳርድ ሚዲያ መስራች የሆኑት ፀዳለ ለማ ከዚህ በፊት ከተለመዱት ጥቃቶች የተለየ እና የጎንዮሽ ጠባይ ያለው ጥቃት እየተስተዋለ ነው፤ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ለዚህ መዘጋጀት ይገባቸዋል ሲሉ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ከዚህ ቀደም የመገናኛ ብዙኃን ከመንግሥት ጋር ስለመብታቸው ይታገሉ እንደነበር የሚያስታውሱት ፀዳለ፤ አሁን ላይ ይህ ተቀይሯል ብለዋል። ይህ በተለይም በበይነ መረቡ ላይ በሰፊው እየታየ መጥቷል ይላሉ።
መንግሥት ጥቃቶችን ወደ ግሉ ዘርፍ በማዘዋወር የሚያደርሰው ጫናም እጅግ እንደሚያሳስባቸው እና መቆም እንዳለበትም ተናግረዋል።
እነዚህ ጥቃቶች ከግለሰቦች፣ ከአንዳድ ተቋማት ብሎም ለመንግሥት ጋር ቅርበት ካላቸው አካላት የሚደርስ ስድብን፣ ማዋረድ ዛቻ እና ማስፈራሪያን ያጠቃለሉ ናቸውም ብለዋል።
አንዳንዴም የሚላኩት መልዕክቶች "ቤተሰብን ጭምር የሚያስፈራሩ" እየሆኑ መምጣታቸውን አንስተዋል።
"ጋዜጠኞቻችን ለዚህ ጉዳይ መዘጋጀት ያለባቸው አዲስ ክስተት ነው። መደረግ የሌለበት ግን እየመጣ ያለ ክስተት ነው። አሁን የተደረገው ነገርም ይህ ነው። አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን 'የእናት ጡት ነካሽ' ሲል በሺዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት ደጋፊዎች እንደዚው ነው የሚረዱት። ሚዲያው ራሱን ከነዚህ አይነት ጥቃቶች ለመከላከል ይህ ትምህርት ነው" ብለዋል።
ስለባለስልጣኑ ውሳኔ
ፀዳለ የአዲስ ስታንዳርድ ሚዲያን ፈቃድ ያገደው የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ሕጉን የጣሰ እንዲሁም ያልታሰበበት ውሳኔ መስጠቱ አስደንጋጭ ነው ይላሉ።
"መሆን የሌለበት፣ ሊፈጠርም የማይገባ ነበር" በማለትም ባለሥልጣኑ አሳልፎት የነበረውን የእገዳ ተግባር ገልጸውታል።
የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣኑ በአዲሱ የሚዲያ ሕግ መሰረት የተሰጠውን ሥልጣን ተላልፎ የአዲስ ስታንዳርድ ሚዲያ አሳታሚ የሆነውን የጃኬን አሳታሚን ፈቃድ አግጃለሁ ማለቱ አግባብ አይደለም ሲል ተቋሙ ባለሥልጣኑን መሞገቱን በይፋ አስታውቋል።
የተቋሙ መስራች ፀዳለ እንደሚሉትም ይህ ፈቃድ የተሰጠው በንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንጂ በባለሥልጣኑ አይደለም፤ ባለስልጣኑ የሰጠው ፈቃድም የኦንላይን ተግባራትን የተመለከተውን ብቻ ነው።
ተቋሙ በሕጉ የሚጠበቅበትን ቅድመ ማስጠንቀቂያ ጨምሮ ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን ሳያሟላ፤ ብሎም ፈቃድን የማገድ ሥልጣንም የቦርዱ ሆኖ ባለሥልጣኑ ያሳለፈው ውሳኔ አግባብ አልነበረም ሲሉም ፀዳለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሕግን የማክበር ተግባር ሕጉን ከሚያስፈፅሙ አካላት መጀመር አለበት ያሉት ፀዳለ "ሕግ አስከባሪው ከሕግ በላይ አይደለም" ሲሉ አክለዋል።
ፀዳለ ይህንን የሕግ ጥሰት ጨምሮ ከዚህ ቀደም በአንድ የተቋሙ ከፍተኛ ባለስሥጣን በአዲስ ስታንዳርድ ላይ በይፋ መሰረት የሌለው እና "የእናት ጡት ነካሽ እና ባንዳ የሚሉ" የሚሉ አስተያየቶችን መሰንዘራቸውን ያስታውሳሉ።
ለባለሥልጣኑም ይህ የሥራ ኃላፊው ይፋዊ አቋም በውሳኔው ላይ ጫና ካለው እንዲጣራ የሚዲያው ኃላፊዎች ከመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣኑ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ጠይቀዋል።
እንዲሁም "የሽብርተኛ ቡድንን አጀንዳ ያራምዳል" የሚለው ክስ ላይም ባለሥልጣኑ ይፋዊ ማብራሪያ እንዲሰጥ፤ ይህ በቀላሉ የማይታይ እና የሠራተኞቹን ሕይወት እና ደኅንነት ጭምር አደጋ ውስጥ የከተተ ክስ ነበርም ብለዋል።
የአዲስ ስታንዳርድ አዘጋጆች ከባለሥልጣኑ ኃላፊ አቶ ኢድሪስ መሐመድ ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ መተማመን ላይ ደርሰዋል። የታገደውን ሰርቲፊኬት መመለስን ጨምሮ ባለሥልጣኑ ያቀረባቸው ክሶች ላይ ማብራሪያ በይፋ እንዲደሚሰጥ ቃል በመግባቱ ረቡዕ ከሰዓት ጀምሮ ወደ ሥራ መመለሳቸውን ፀዳለ ተናግረዋል።
በተሻሻለው የመገናኛ ብዙኃን ሕግ መሰረት አንድ የብሮድካስት ባለ ፈቃድ የተከለከሉ ተግባራትን በተደጋጋሚ የሚጥስና የጥሰቱም ክብደት እየጨመረ መምጣት ማሻሻያ እንደማያደርግ የማያሳይ ከሆነ ባለሥልጣኑ ፈቃዱን ከአንድ ወር ላልበለጠ ጊዜ ሊያግድ እንደሚችል ደንግጓል።
አዋጁ የፈቃድ መሰረዝ፣ የፈቃድ ማደስ ወይም የፈቃድ መታገድን የተመለከቱ ተግባራት የሚያስከትሉ ውሳኔዎችን የመወሰን ሥልጣን የባለሥልጣኑ ቦርድ እንደሆነም ይደነግጋል።
የሚዲያ ነፃነት
ፀዳለ ለሦስት ዓመታት በበርካታ ባለሞያዎች በብዙ ልፋት የፀደቀው የሚዲያ ሕግ መሻሻሉ ለመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ስኬት እንደሆነ ያምናሉ።
ሕጉ "ያልተገደበ፣ ነገር ግን በብዙ ኃላፊነት የተሞላ መብት የሚሰጥ መሆኑን አይተን እኛም እንደ-ሚዲያ የተለያዩ የማስፋፊያ ሥራዎች ውስጥ ገብተናል፤ ሕጉን አምነን" ይላሉ።
ነገር ግን ሕጉን ማስፈፀም ባለበት አካል እንዲህ አይነት ውሳኔ መወሰኑ አስደንጋጭ መሆኑንም ይናገራሉ። ተቋማቸው ሥራ አቁሞ የነበረውም ይህ ጉዳይ ባግባቡ ሊታይ ስለሚገባው እንደሆነም ያክላሉ።
የኢትዮጵያ ሚዲያ ለረጅም ዓመታት ከእንደዚህ አይነት ነገሮች ለመውጣት በርካታ ዓመታት ታግሏል የሚሉት ፀዳለ፤ አሁን በሕግ የወጣውን መጣስ ያንን አለማክበር ነው ብለዋል።
እናም ሕጉን አለማክበር "ወደ ኋላ መዘፈቅ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
"በግሌ መንግሥትን መተቸት ሕገ መንግሥታዊ መብቴ ነው"
የፈቃድ መታገዱ የሚዲያው መስራች በይፋ በመንግሥት ላይ በሚያቀርቧቸው ትችቶች የመጣ ይሆን? ወይ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ፀዳለ "አዲስ ስታንዳርድ ተቋም ነው፣ በግሌ የማቀርበው ትችትም ቢሆን ሕገ መንግሥታዊ መብቴ ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥጠውበታል።
"እኔ በይፋ በምናገረው ትችት ሚዲያውን መዝጋት ምን ማለት ነው? አንድ ሰው አንድን መንግሥት መተቸት አይችልም ማለት ነው? ሕገ መንሥታዊ መብቴ ነው። ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ እናደርጋለን ከተባለ የመጀመሪያው ተግባር ግለሰቦች ከመንግሥት ጋር በሃሳብ ያለመስማማት መብታቸውን ማክበር ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"አዎ! እኔ ኮንፈርሚስት [በሁሉም ነገር ተስማሚ] አይደለሁም፤ አልነበርኩም ወደፊትም አልሆንም፡፡ በህወሓት ኢሕአዴግ ጊዜም ተቺ ነበርኩ። ያ ሚዲያን ሊያዘጋ የሚችለው እንዴት ነው? ሕግ እና ሥርዓት ያለበት አገር ነው" ብለዋል።
በትግራይ ክልል ያለው ጦርነትንም ከመጀመሪያው ጀምሮ ሲቃወሙ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ "ከመጀመሪያው ቀን ጀምረው ሲደግፉ የነበሩ ሰዎች አሉ፤ እንዲህ አይነት ችግር ደርሶባቸዋል ወይ?" ሲሉም ጠይቀዋል።
"በሃሳብ መለያየት ላይ ተመስርቶ የአንዳድ ሰዎች መብት የሚጠበቅበት፤ የሌሎች የማይከበርበት ሥርዓት መመስረት የለበትም። ይሔ ሁሉ ትጋት፣ ጥረት እና ይሄ ሁሉ ሰው መሞት ከኢሕአዴግ የባሰ መንግስት ለመመስረት አይደለም። መንግሥት የሚቃወሙትን ሰዎች የሚደግፉትን ሰዎች ያህል ማክበር ሲችል ነው የተሻለ ነገር መመስረት የሚቻለው" ሲሉም ፀዳለ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
በይፋ በሚሰጧቸው አስተያየቶች ምክንያት ሚዲያውን ለመዝጋት ታስቦ ከሆነም አግባብ ያልሆነ ተግባር ነው ሲሉም አክለዋል።
አዲስ ስታንዳርድ ከ12 ዓመታት በፊት ወርሃዊ የእንግሊዝኛ መፅሄት ሆኖ የተቋቋመ ሲሆን ከአምስት ዓመት በፊት ታውጆ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባስቀመጣቸው አሳሪ አሰራሮች ምክንያት ሥራውን ሙሉ በሙሉ በይነ መረብ ተመስርቶ እያከናወነ ይገኛል።












