ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ ከ20 ዓመታት በኋላ 'የመዘንጋት በሽታ' መድሃኒት ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቀደች
የአሜሪካ የመድሃኒት ተቆጣጣሪዎች ከ20 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያውን የ'አልዛይመር' መድሃኒት ስራ ላይ እንዲውል ፈቅደዋል።
ይህም በዩናይትድ ኪንግደም ተመሳሳይ ውሳኔ እንዲያልፍ በር የከፈተ ነው ተብሏል።
'አዱካኑማብ' የተሰኘው ይህ መድሃኒት 'የመዘንጋት በሽታ'ን ምልክቶች ከማከም ይልቅ የበሽታው ስረ-መሰረት ላይ በማነጣጠር መፍትሄ እንደሚሰጥ ነው የሚታመንበት።
የዚህን መድሃኒት ጥቅም ላይ መዋል በአሜሪካ ላሉ የበጎ አድራጎት ተቋማት መልካም ዜና ሆኗል።
በተቃራኒው የህክምና ልሂቃን መድሃኒቱ የሙከራውን ውጤት መነሻ በማድረግ በመድሃኒቱ ወጤታማነት ላይ ተመሳሳይ አቋም አላንጸባረቁም።
የአሜሪካ የምግብ እና የመድኃኒት ቁጥጥር አስተዳደር 'አዱካኑማብ' በአንጎል ውስጥ የሚገኙትን 'የአሚሎይድ ቤታ' እንደሚቀንስ ተጨባጭ ማስረጃዎች መኖራቸውን አስታውቋል።
ይህም "ለታካሚዎች ያለውን ጠቀሜታ ለመተንበይ አስፈላጊ መነሻ ነው" ብሏል።
እንደ አውሮፓውያኑ በመጋቢት 2019 300 ታካሚዎች በተሳተፉበት በየወሩ በፈሳሽ መልክ በአፍ የሚወሰደው 'አዱካኑማብ' ቅድመ ሙከራ ላይ የታየው ውጤት ከሌሎች የ 'ዱሚ መድሃኒቶች' አንጻር የማስታወስና የማሰብ ችግረን በመፍታት በኩል የተሻለ ሆኖ አልተገኘም።
ሆኖም በዛው ዓመት መጨረሻ በአሜሪካ የሚገኘው የመድሃኒቱ አምራች ከባንያ 'አዱካኑማብ'ን በመጠን ከፍ ተደርጎ ከተወሰደ ውጤት ያመጣል ሲል ገልጿል። ኩባንያው መድሃኒቱ የማወቅ [ኮግኒቲቭ] ማሽቆልቆልን በእጅጉ ይቀንሳል ብሏል።