በካናዳ የተገኘው የ215 ህፃናት ጅምላ መቃብር ቁጣን አስነሳ

ከሰሞኑ የ215 ህፃናትን አፅም የያዘ የጅምላ መቃብር መገኘቱን ተከትሎ በካናዳ የሚገኙ የቀደምት ህዝቦች ማህበራት አገር አቀፍ ፍለጋው እንዲጀመር ጠይቀዋል፤ ቁጣቸውንም እየገለፁ ነው።

የቴኬኤምሉስፕ ቴ ሴክዌፑምክ ቀደምት ህዝቦች መሪ በያዝነው ሳምንት እንዳሳወቁት የህፃናቱ አፅም የተገኘበት ስፍራ የቀድሞ አዳሪ ትምህርት ቤት ሲሆን የተቋቋመውም ቀደምት ህዝቦችን ወደ ነጭ ባህል ለማላመድ በሚል አላማ ነው።

የህፃናቱ አፅም የተገኘው ካምሎፕስ ኢንዲያን በተባለ አዳሪ ትምህርት ቤት ሲሆን ትምህርት ቤቱ በአውሮፓውያኑ 1978 ተዘግቷል።

እነዚህ ትምህርት ቤቶች የቀደምት ህዝቦች ልጆች በአዳሪነት ይማሩባቸው የነበሩ ናቸው።

ከአውሮፖውያኑ 1863-1998 150 ሺህ የሚሆኑት እነዚህ ህፃናት ከቤተሰቦቻቸው በአስገዳጅ ሁኔታ ተወስደው በነዚህ ትምህርት ቤቶች ይማሩ ነበር።

በራሳቸው ቋንቋ መናገርም ሆነ ባህላቸውን እንዲከተሉ አይፈቀድላቸውም ነበር፤ ከፍተኛ ጥቃቶችንም አስተናግደዋል።

የጅምላ መቃብር መገኘቱ በርካቶችን ያስቆጣ ሲሆን ብዙዎችም በጊዜያዊነት በተሰራው የህፃናቱ መታሰቢያ ላይ ትንንሽ ጫማዎችን በማስቀመጥ ለማስታወስም ሞክረዋል።

የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ እንደሚረዱ ቃል ቢገቡም ዝርዝር ከመስጠት ተቆጥበዋል።

"እንደ አባት ልጆቼ በአስገዳጅ ሁኔታ መወሰድን ማሰብ ይከብዳል" በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሪፖርተሮች ተናግረዋል።

አክለውም "እንደ ጠቅላይ ሚኒስትርም የቀደምት ህዝቦችን ህፃናትን ከማህበረሰቡ በመስረቅ ላይ የተመሰረተው ይህ የማላመድ ፖሊስ ምን ያህል አሳፋሪ እንደሆነ ልገልፅ እፈልጋለሁ" ብለዋል።

ጀስቲን ትሩዶ ከሪፖርተሮች መንግሥታቸው ምን ያደርጋል? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ጠንከር ያለ እርምጃ እወስዳለሁ ቢሉም ዘርዘር ያለ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የቀደምት ህዝቦች ጉባኤ ብሔራዊ መሪ ፔሪ ቤልግሬድ ባወጡት መግለጫ ቤተሰቦች እውነታውን ማወቅ እንደሚገባቸውና ከሃዘናቸውም ለማገገም እድሉን ሊያገኙ ይገባል ብለዋል።

"በቀድሞ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ላይ ምርመራዎች ቢካሄዱ በህዝቦቻችን ላይ የደረሱ በርካታ የዘር ጭፍጨፋዎችን እውነታ እንረዳለን" በማለት ፔሪ ገልፀዋል።

የህፃናቱን የጅምላ መቃብር መገኘት ተከትሎ በቻርሎቴ ታውን በተባለችው ግዛት የመጀመሪያ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆን ኤ ማክዶናልድ ሃውልት ተገርስሷል።

ማክዶናልድ በነዚህ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ላይ በነበራቸው ከፍተኛ ሚናም ነው ተቃዋሚዎች ሃውልቱን ኢላማ ያደረጉት።

ካምሉፕስ ኢንዲያን አዳሪ ትምህርት ቤት የነጮችን ባህል ለማላመድ ከተከፈቱ ትምህርት ቤቶች መካከል ትልቁ ነው።

በሮማን ካቶሊክ አስተዳደር የበላይነትም ሲሆን የተከፈተው ወቅቱም በአውሮፓውያኑ 1890 ነው። የተማሪዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው በተባለበት በአውሮፓውያኑ 1950ዎቹ 500 ተማሪዎችን ተቀብሎ ያስተናግድ ነበር።

ማዕከላዊው መንግሥት በአውሮፓውያኑ 1969 የማስተዳደሩን ሁኔታ ከተቀበለ በኋላ ለአካባቢው ተማሪዎች እንደ አዳሪ ትምህርት ቤት ይገለገሉበት የነበረ ሲሆን በ1978ም ተዘግቷል።