ራፐር ዲኤምኤክስ ባጋጠመው የልብ ህመም ምክንያት ሆስፒታል ገባ

አሜሪካዊው የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ እና ተዋናይ ዲኤምኤክስ የልብ ህመም አጋጥሞት ሆስፒታል መግባቱን ጠበቃው ሙሪ ሪችማን ተናገሩ።

ሪችማን ለአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን እንደገለጸው ድምጻዊውን ያጋጠመው የልብ ህመም ከፍተኛ መጠን ያለው መድኃኒት ከመውሰድ ጋር የተያያዘ ይሆን አይሆን እንደማያውቅ መናገሩን ቲኤምዚ ዘግቧል።

ዲኤምኤክስ ለዓመታት ከአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነት ጋር ሲታገል የነበረ ሲሆን በተደጋጋሚ ወደ ማገገሚያ ገብቶ ነበር።

በአድናቂዎቹ የሂፕ ሆፕ ታላቅ ሰው ተደርጎ የሚታየው ራፐሩ፣ ፊልሞች ላይ ከመሳተፍ በተጨማሪ ከጄይ ዚ፣ ጃ ሩል፣ ኢቭ እና ኤልኤል ኩል ጄ ጋር በጋራ የተለያዩ ሙዚቃዎችን ተጫውቷል።

ዲኤምኤክስ በሙያው ከ20 ዓመት በላይ የቆየ ሲሆን ክሬድል 2 እና ሮሚዮ መስት ዳይ ፊልሞች ላይ ከጄት ሊ ጋር ተውኗል።

የ50 ዓመቱ ራፐር የመታወቂያ ስሙ አርል ሲመንስ ሲሆን ሆስፒታል የገባው አርብ ማታ መሆኑን ጠበቃው አክሎ ተናግሯል።

በዙሪያው ቤተሰቦቹ መኖራቸውንም ገልፀዋል።

"በመተንፈሻ መሳሪያ ታግዞ ነበር የሚተነፍሰው፤ አሁን ግን እርሱ ተነቅሎ በራሱ እየተነፈሰ ነው" ብሏል ጠበቃው።

የ15 ልጆች አባት የሆነው ራፐሩ ከዚህ ቀደም የጦር መሳሪያ እና አደንዛዥ ዕፅ በመያዝ፣ በግዴለሽነት በማሽከርከርና በእንስሳት ላይ ያልተገባ ነገር በመፈጸም እስር ቤት ገብቶ ያውቃል።

እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2018 በታክስ ማጭበርበር ተከስሶ ችሎት ፊት በቀረበበት ወቅት ከሙዚቃ ሥራዎቹ መካከል አንዱን ለዳኛው በመጫወት የመገናኛ ብዙሃን ደጋግመው ስሙን ያነሱት ነበር።

በወቅቱ ዳኛው ሙዚቃውን ካዳመጡ በኋላ ዲኤምኤክስ "መልካም ሰው ነው" በማለት የአንድ ዓመት እስር ብቻ ፈርደውበታል።

በ2016 ደግሞ በኒው ዮርክ ከተማ በሚገኝ አንድ ሆቴል የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ላይ ሳለ ለመተንፈስ ተቸግሮ የህክምና እርዳታ ለማግኘት ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ነበር።

ጠበቃው "አርል በጣም መልካመ ሰው ነው፤ ታሪክ መናገር የሚችል እጅግ መልካም ሰው" በማለት በደረሰበት የጤና መታወክ የተሰማውን ሐዘን ገልጿል።