በኬንያ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጆች በሴት ጥቃት ላይ በመሳለቃቸው ከሥራ ተባረሩ

የፎቶው ባለመብት, HOMEBOYZ RADIO
በኬንያ ሦስት የሬዲዮ ፕሮግራም አሰናጆችና የሙዚቃ አጫዋቾች (ዲጂዎች) ሥራቸውን አጥተዋል።
ምክንያቱ ደግሞ በቀጥታ በተላለፈ ሥርጭት ላይ 'ሴቶች ጥቃት ቢደርስባቸው ጥፋቱ የራሳቸው ነው እንጂ የወንዱ አይደለም' ብለው በመከራከራቸው ነው።
እነዚህ ሦስት የሬዲዮ የውይይትና የሙዚቃ ፕሮግራም አዘጋጆች የውይይት መነሻ አንድ በፍርድ ቤት የተያዘ ጉዳይ ሲሆን ሰውየው በፌስቡክ ያገኛትን ሴት በመጀመርያ የፍቅር ግንኙነታቸው ባለመግባባታቸው ከ12ኛ ፎቅ ላይ ገፍትሮ በመጣል ለመግደል ሙከራ ስላደረገበት ሁኔታ ነበር ያወያዩ የነበሩት።
በዚህ ውይይታቸው ታዲያ ለዚህ ጥቃት ተጠያቂዋ ራሷ ሴቷ ናት እያሉ ሲሳለቁ ነበር።
ይህ ሁኔታ ያስቆጣቸው አድማጮች ጉዳዩን ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ በመውሰዳቸው ቁጣ ተቀስቅሶ ነው ከሥራ ለመባረር የበቁት።
የኬንያ ባለሥልጣናት እንዳሉት የሬዲዮ ፕሮግራሙ አዘጋጆቹ አስተያየት የሴቶች ጥቃትን የሚያበረታታ በመሆኑ ፕሮግራሙ ለጊዜው እንዲታገድ አድርገዋል።
ኢዩኒስ ዋንጋሪ የተባለችው ሴት ሞሴስ ጌታም ከተባለ ሰው ጋር በፌስቡክ ከተዋወቁ በኋላ ነበር የመጀመሪያ ቀጠሮ የያዙት።
በፍቅር ቀጠሯቸው ወቅት ወሲብ ለመፈጸፍ ፍላጎት ያደረበት ወንዱ ጥያቄ ሲያቀርብ ሴቷ ፍቃደኛ ባለመሆኗ ከ12ኛ ፎቅ መስኮት ላይ ገፍትሮ ለመጣል ሙከራ ያደረገው።
ሰውየው ጥፋተኛ አይደለሁም ሲል ለፍርድ ቤት የተናገረ ሲሆን ጉዳዩ አሁንም በፍርድ ሂደት ላይ ይገኛል።
ባለፈው ረቡዕ በሆምቦይዝ ሬዲዮ 'ሊፍት ኦፍ' በተሰኘ ልዩ ፕሮግራም ላይ የቀረቡት አዘጋጆቹ ለክስተቱ ተጠያቂዋ እሷ እንጂ ገፍትሮ ሊጥላት የሞከረው ሰውዬ አይደለም ሲሉ ተሳልቀዋል።
የሬዲዮ ፕሮግራሙ አዘጋጅ የሆነውን ታሪክ ካቀረበ በኋላ "ለመሆኑ ኬንያዊያን ሴቶች በቀላሉ የምትገኙ፣ በቀላሉ እሺ የምትሉ፣ ወንድ ለማግኘት የማትፈነቅሉት ድንጋይ አለመኖሩ ለምን ይሆን? ይሄን ያህል ወንድ ለማግኘት ሰፍሳፋ ለምን ሆናችሁ?" ሲል ያልተገባ አስተያየት ሰንዝሯል።
ይህ ያልተገባ ንግግሩ ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ ተወስዶ ቁጣ ከቀሰቀሰ በኋላ የዚህ መሰናዶ ማስታወቂያ አስነጋሪዎች ኮንትራታቸውን መሰረዛቸው ተሰምቷል።
ጊነስ ቢራን አምራቹ ኢስት አፍሪካ ብሪወሪስ፤ የአዘጋጁ ንግግር ሴቶቸን ለሚፈጸምባቸው ጥቃት ተጠያቂ ስለሚያደርግ ቅር መሰኘቱን በመግለጽ ማስታወቂያ በዚያ ራዲዮ ላለማስነገር ውሳኔ ላይ መድረሱን አሳውቋል።
የዚህ መሰናዶ አዘጋጅ በኢኒስታግራም ገጹ ላይ የኬንያን ሴቶችን በይፋ ይቅርታ ጠይቋል።
ሆኖም ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ሆምቦይዝ ሬዲዮ ሦስቱን ዲጂዎች ከሥራ አባሯቸዋል።
ፕሮግራማቸውም ለ6 ሳምንታት ከአየር እንዲወርድ የተወሰነ ሲሆን የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ደግሞ ሬዲዮ ጣቢያውን የአንድ ሚሊዮን ሺሊንግ [ከዘጠን ሺህ ዶላር በላይ] ቅጣት ጥሎበታል።












