ኮሮናቫይረስ ፡ ደቡብ አፍሪካ የኮቪድ-19 ክትባትን ለፕሬዝዳንቷ በመስጠት ጀመረች

የፎቶው ባለመብት, @CyrilRamaphosa
ደቡብ አፍሪካ ለፕሬዝዳንቷ ሲሪል ራማፎሳ ቅድሚያ በመስጠት የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የኮሮናቫይረስ ክትባትን መስጠት ጀመረች።
ፕሬዝዳንቱ በኬፕታውን በካይየሊትሻ አቅራቢያ በሚገኘው ሆስፒታል መገናኛ ብዙኃን ፊት ተከትበዋል።
በኋላም በትዊተር ገጻቸው ብቅ ብለው "ክትባቱን መውሰድ ፈጣን፣ ቀላል እና የማያም ነው" ሲሉ አስፍረዋል።
"የጤና ባለሙያዎች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በመጀመሪያ ረድፍ ስለሚሰለፉ ክትባታቸውን ለመቀበል እንዲመዘገቡ አሳስባለሁ" ሲሉ መልዕክታቸውን አስቀምጠዋል።
80 ሺህ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የኮሮናቫይረስ ክትባት ማክሰኞ ምሽት አገሪቱ ደርሷል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዝዌሊ ምኪዤ እና ሌሎች የጤና ባለሙያዎችም ከመጀመሪያዎቹ ተከታቢዎች መካከል ሆነዋል።
"ቀኑ ለእኛ ደቡብ አፍሪካውያን አዲስ ምዕራፍን ይወክላል። በመጨረሻም ክትባቶቹ ደርሰው ለሰዎች እየተሰጡ ነው" ብለው ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ከተከተቡ በኋላ ተናግረዋል ሲል ኒውስ 24 የተባለው ድረ ገጽ አስነብቧል።
ኮሮናቫይረስ በአፍሪካ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ የደቆሳት ደቡብ አፍሪካ ክትባቱን መጀመር ያቀደችው ባለፈው ሳምንት ነበር።
የአስትራዜኔካ ክትባት በፍጥነት በሚሰራጨው የኮሮናቫይረስ አዲሱ ዝርያ ላይ ውጤታማ ላይሆን ይችላል የሚል ስጋት በመፍጠሩ ምክንያት ዘግይቷል፡፡
የጆንሰን እና ጆንሰን ክትባት የአንድ ጊዜ ብቻ የሚሰጥ ሲሆን ለመስጠትም በጣም ቀላል ነው ተብሏል፡፡












