መንግሥት የአውሮፓ ሕብረት መግለጫ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ ነው አለ

የፎቶው ባለመብት, MOFA
የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር የአውሮፓ ሕብረት በትግራይ ክልል ከሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ጋር በተገናኘ ያወጣው መግለጫ በትግራይ ያለውን ተጨባጭ እውነታን ያላገናዘበ ከመሆኑም በላይ የኢትዮጵያ መንግሥት በክልሉ እያቀረበ ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍ ከግንዛቤ ያላስገባ ነው ብሏል።
የአውሮፓ ሕብረት ትናንት ባወጣው መግለጫ በትግራይ እየተፈጠረ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ እጅጉን አሳስቦኛል ብሏል። ሕብረቱ በመግለጫው የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢያዎች ክልከላ እንዳይደረግባቸውና መንግሥት ለስደተኞችና ሲቪሎች ጥበቃ እንዲሰጥ ጠይቋል።
የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር በበኩሉ "መንግሥት በአካባቢው የሕግ ማስከበር ስራን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሕብረቱ የሚያወጣው መረጃ ሚዛናዊነቱን ያልጠበቀ እና ተገቢነት የሌለው ነው" ብሏል።
የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦቱ በበርካታ የትግራይ ክልል ተደራሽ እንዲሆን መንግሥት እየሰራ ነው፤ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች እንዲጎበኝ ተደርጓል ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ 4.5 ሚሊየን ሕዝብ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልገዋል ማለቱ ይታወሳል።
ከቀናት በፊት ትግራይ የገቡት የዓለም ምግብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቢዝሊይ የኢትዮጵያ መንግሥት እና እርሳቸው የሚመሩት ድርጅት በመላው ትግራይ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ከስምምነት መድረሱን ከቀናት በፊት አስታውቋል።
ዴቪድ ቢዝሊይ "በትግራይ ሦስት ሚሊዮን ሕዝብ የእኛን አስቸኳይ እርዳታ ይሻል። የምናባክነው ጊዜ የለም" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በትግራይ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር 2.5 ሚሊዮን ነው ሲል ቆይቷል። የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ትናንት በሰጡት መግለጫ 2 ሚሊዮን ለሚሆን ሕዝብ የሰብዓዊ እርዳታ መቅረቡን ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜና የኖርዌጂያን ሪፊዉጂ ካውንስል በህጻጽ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለመስጠት ያስገነባቸው ግንባታዎች በእሳት እንዲወድሙ መደረጉን አስታውቋል።
የሳተላይት ምስሎች ግንባታዎች የወደሙት ከታኅሣሥ 27 እስከ ታኅሣሥ 30 ባሉት ቀናት መሆኑን ካውንስሉ አስታውቋል።
መንግሥት በበኩሉ የኤርትራውያን ስደተኞች ማቆያ የነበሩትን ህጻጸ እና ሽመልባ መጠለያ ጣቢያዎች በቅርቡ እንደሚዘጉ የስደት እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ትናንት በሰጠው መግለጫ ላይ አስታውቋል።
ሽመልባ የተመሰረተበት ቦታ ከኢትዮ-ኤርትራ ድንበር በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ ለመዘጋቱ በምክንያትነት ሲጠቀስ፣ በበረሃማ ቦታ የሚገኘው ህጻጽ፤ ለኑሮም ሆነ ለስደተኞች መጠለያነት አመቺ ባለመሆኑ በተመሳሳይ እንደሚዘጋ ኤጀንሲው ገልጿል።
የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር እነዚህን ሁለት የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ከዚህ ቀደምም ለመዝጋት ታስቦ ክልሉን በሚመራው ህወሓት አለመፍቀድ ሳይዘጉ ቀርተዋል ብሏል።
የውጪ ጉዳይ ሚንሰቴር ኢትዮጵያ ከ27 የተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ከ1 ሚሊየን በላይ ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች መሆኗን አስታውሶ፤ ኤርትራውያን ስደተኞችም አለም ዓቀፍ መብታቸው ተከብሮ በተመሳሳይ በኢትዮጵያ እየኖሩ ይገኛሉ ብሏል።
"የኤርትራ ጦር ትግራይ ለቆ ይውጣ"
የአውሮፓ ሕብረት በትናንትናው መግለጫው የኤርትራ ጦር ከትግራይ እንዲወጣም ጠይቋል። ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ የአሜሪካ ስቴትስ ዲፓርትመንት የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ ለቆ እንዲወጣ መጠየቁ ይታወሳል።
የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር በትናንትናው መግለጫው በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው ነገር ባይኖርም፤ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግሥትም የኤርትራ ባለስልጣናት የኤርትራ ጦር በትግራዩ ግጭት ተሳትፎ አላደረገም ብለዋል።












