ፖፕ ፍራንሲስ በሲኖዶሱ ከፍተኛ አመራር አድርገው የመጀመሪያዋን ሴት ሾሙ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የሮማ ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ በሲኖዶሱ ውስጥ ከፍተኛ የተባለውን ሹመት ለሴት ሰጥተዋል።
በሲኖዶሱ ውስጥ ከፍተኛ አመራር ውስጥ የተቀመጡ የመጀመሪያ ሴት ሆነዋል።
ትውልዳቸው ከፈረንሳይ የሆኑት ናታሊ ቤኳርት በሲኖዶሱ ውስጥ የመምረጥ መብት ይኖራቸዋል ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ ፖፑን ማማከር እንዲሁም በሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አወዛጋቢ ለሚባሉ ጉዳዮችም ቤተ ክርስቲያኗ ምን አይነት ውሳኔ ማሳለፍ አለበት ለሚለውም አንድ አማካሪና ወሳኝ ይሆናሉ።
ናታሊ ቤኳርት ከአውሮፓውያኑ 2019 ጀምሮ ሲኖዶሱን በማማከር ሰርተዋል።
የሲኖዶሱ ዋና ፀሃፊ ካርዲናል ማሪዮ ግሬች ሹመቱ "በሩ እንደተከፈተ ማሳያ ነው" ማለታቸው ተዘግቧል።
የፖፑ ውሳኔ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ቁልፍ የሚባሉ ውሳኔዎች ላይ የሴቶች ተሳትፎን በከፍተኛ ሁኔታ ለመጨመር ያላቸውን ፍላጎት የሚያሳይ ነው ብለዋል ዋና ጸሃፊው
ምንም እንኳን ይሄ ውሳኔ ሴቶችን የቅስና ማዕረግ ለመስጠት ጠቋሚ ባይሆንም የፖፑ ተችዎች የቅስና ማዕረግ ከመስጠት አቅጣጫ ጋር ሊያገናኙት እንደሚችሉ የቢቢሲው ጆን ማክ ማኑስ ዘግቧል።
ከናታሊ በተጨማሪ ስፔናዊው ቄስ ሉዊስ ማሪን ደ ሳን ማርቲን በሲኖዶሱ ከፍተኛ ሹመት የተሰጣቸው ሌላኛው ሰው ናቸው።
በቅርብ ዓመታት የጳጳሳቱ ሲኖዶስ ከፍቺ ጋር የተያያዙ የቀኖና ዶግማዎች ምን መሆን አለበት በሚለው ተወያይቷል።
ፖፕ ፍራንሲስ ከሰሞኑ የሮማውን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ህግ በመቀየር ሴቶች ቁርባንን ጨምሮ ሌሎች የቤተ ክርስቲያኗን አገልግሎቶችን እንዲያካሂዱ ፈቅደዋል።
በተቀየረው ህግም መሰረት ሴቶች ቤተ መቅደሱ ውስጥ ሆነው ማገልገልም ይችላሉ።
ሆኖም የተቀቡት ቄስ በበላይነት ስርዓቱን እንደሚቆጣጠሩ አፅንኦት ሰጥተዋል።
በተለያዩ በምዕራባውያን አገራት በሚገኙ የካቶሊክ አብያተ ክርስትያናት ውስጥ ሴቶች እነዚህን አገልግሎቶች የሚያከናውኑ ሲሆን የፖፑ የአሁኑ ውሳኔ ለነዚህ ስፍራዎች እውቅናን እንዲያገኙ ሆኗቸዋል።
ባለፈው አመት እንዲሁ ፖፑ የቫቲካንን የገንዘብ ሁኔታ በበላይነት የሚቆጣጠረው ምክር ቤት ስድስት ሴቶችን ሾመዋል።












