በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲ ላይ ጥቃት ሊፈጽሙ ነበሩ የተባሉ በቁጥጥር ስር ዋሉ

የፎቶው ባለመብት, NISS
በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲ ላይ ጥቃት ለመፈፀም በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ ነበሩየተባሉ 15 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ።
ይህ የተባለው የብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ ነው።
የብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን በኤምባሲው ላይ ጥቃት በመፈጸም በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ እንዲሁም የአዲስ አበባን ገፅታ ለማበላሸት በዝግጅት ላይ የነበሩ ናቸው ያላቸውን 15 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።
ሬውተርስ በጉዳዩ ላይ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር አስተያየት ቢጠይቅም ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል።
አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ በህቡዕ የተደራጀው ቡድን ጥቃቱን ለመፈጸም ተልዕኳቸውን ከውጭ መቀበላቸውን እና ለጥቃት ሊጠቀሙባቸው ያዘጋጇቸው ከፍተኛ የጦር መሣሪያዎችና ተቀጣጣይ ቁሳቁሶች እና ሰነዶች መገኘታቸውን አመልክቷል።
ጥቃቱን ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት መካከል የቡድኑን አባላት ሲመራ ነበር የተባለው የ35 ዓመት ግለሰብ ከፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመር ቢሮ ጋር በመቀናጀት በቁጥጥር ሥር እንዲውል መደረጉን መግለጫውአመልክቷል።
ይህ ጥቃት ለማድረስ የተሰማሩ ቡድን አባላትን ሲመራ ነበር የተባለው ግለሰብ ለጥቃቱ ማቀነባበሪያነት እንዲውል በአሥር ሺዎች የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር ከውጪ እንደተላከለት ከተሰበሰቡ መረጃዎች ማረጋገጥ እንደቻለ የብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት አስታውቋል።
ሌላ ተመሳሳይ ተልዕኮ የተሠጠው ህቡዕ ቡድንም በሱዳን ካርቱም በሚገኘው የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲ ላይ ተመሳሳይ ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን የጠቆመው መግለጫው፤ መረጃውን ቀድሞ ያገኘውና ክትትል ሲያደርግ የቆየው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የግንኙነት መረቡን ለመበጣጠስ እንዲሁም ተጠርጣሪዎችን አድኖ ለመያዝም ከሱዳን የመረጃና የደህንነት ተቋም ጋር በቅንጅት መሰራቱን ጠቁሟል።
በህቡዕ የተደራጀው ቡድኑ መሪ ኑሮውን በስዊዲን ያደረገው ግለሰብ መሆኑን እና ግለሰቡም በስዊዲን አገር በቁጥጥርሥር እንዲውል መደረጉን የብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ገልጿል።
ሌሎች ከሴራው ጋር ግንኙነት ያለቸውና በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ 21 ተጠርጣሪ ግለሰቦችንም በቁጥጥር ሥርየማዋሉ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫአመልክቷል።












