የተከተቡ ሰዎች ኮሮናቫይረስ ሊያስተላልፉ ይችላሉ-እንግሊዛዊው ተመራማሪ

ኮሮናቫይረስ ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Science Photo Library

የምስሉ መግለጫ, ኮሮናቫይረስ ክትባት

በተለያዩ አገራት የኮሮናቫይረስ ክትባት ተጀምሯል። ይሁንና የኮሮናቫይረስ ክትባት የወሰዱ ሰዎች አሁንም ቫይረሱን ለሌሎች ሰዎች ሊያስተላልፉ እንደሚችሉ እየተነገረ ነው።

ይህንን ተከትሎም የእንግሊዝ ምክትል የሕክምና ኃላፊ የተጣሉ ገደቦች መቀጠል እንዳለባቸው አስጠንቅቀዋል።

ፕሮፌሰር ጆናታን-ታም የተባሉ ምሁር ለቴሌግራፍ በጻፉት መልዕክት "ክትባቱ እስካሁን ወደ ሌሎች ሰዎች ማስተላለፍም ሆነ አለማስተላለፉ አልተረጋገጠም" ብለዋል።

በእርግጥ ክትባቱ ተስፋ አጭሯል፤ ነገር ግን በአዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር የግድ በፍጥነት ሊቀንስ ይገባል ብለዋል። ማት ሃንኮክ እንደሚሉት በእንግሊዝ ከ80 ዓመት እድሜ በላይ ካላቸው ሰዎች መካከል ቢያንስ ከ75 በመቶ በላይ የሚሆኑት መከተባቸውን ገልጸዋል።

የኮሮናቫይረስ ክትባት ሁለት ጊዜ የሚሰጥ ሲሆን አሁን ያለው መረጃ የሚያሳየው ግን አንድ ጊዜ ብቻ የወሰዱትን ነው። የእንግሊዝ የጤና ሚንስትር ለስካይ ኒውስ እንደገለጹት ከሆነ በቤት ውስጥ እንክብካቤ ከሚገኙ ሰዎች መካከል ሦስት አራተኛ የሚሆኑት መከተባቸውን ገልጸዋል።

"ፈረንሳይ አጠቃላይ ከከተበችው በላይ ባለፉት ሦስት ቀናት እኛ ከትበናል" ብለዋል ሚስተር ሃንኮክ።

በእዚህ ሳምንትም ተጨማሪ 32 የመከተቢያ ጣቢያዎች በመላው እንግሊዝ ይከፈታሉ ተብሏል። ፕሮፌሰር ቫን-ታም እንደሚሉት ደግሞ "የትኛውም ክትባት 100% እንደሚከላከል አልተረጋገጠም። እናም ዋስትና ያለው መከላከያ የለም" ብለዋል።

ክትባቱ ከተሰጠ ጊዜ ጀምሮ ባሉት ሁለት-ሦስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ የማስተላለፍ እድል ሊኖር ይችላል። ስለዚህ በተለይ ለአረጋዊያን ሦስት ሳምንታትን መስጠት ተገቢ ነው ይላሉ።

"ሁለቱንም ክትባት ሰዎች ከወሰዱ በኋላም ቫይረሱን ለሌሎች ሰዎች ሊያስተላልፉ ይችላሉ። በዚህ ምክንያትም የቫይረሱ ስርጭት ሊቀጥል ይችላል" ብለዋል ፕሮፌሰር ቫን-ታም።

"በመሆኑም ሰው ተከትቤያለሁ በሚል እሳቤ ጥንቃቄ ማድረጉን ከተወ ቫይረሱ ወደ ሌሎች ሰዎች መተላለፉን ስለማያቆም ያልተከተቡትን አደጋ ላይ መጣሉ አይቀርም" በማለት አስጠንቅቀዋል።

በእዚህ ሳምንት የህክምና ሞያተኞች በፋይዘር-ባዮንቴክ ሁለት ክትባቶች አወሳሰድ መካከል ያለውን ልዩነት እንዲያጠቡ የጤና ባለስልጣናትን ጠይቀዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም ብዙ ሰዎች የመጀመሪያውን ሕክምና እንዲያገኙ በሚል እሳቤ ሁለቱን ክትባቶች የሚያገኙበት ጊዜ ከሦስት ሳምንት ወደ አስራ ሁለት ሳምንት ከፍ እንዲል ተደርጎ ነበር።

ነገር ግን የእንግሊዝ የጤና ማሕበር ፖሊሲውን "ምክንያታዊ ለማለት ያስቸግራል" በማለት ልዩነቱ ቢያንስ በስድስት ሳምንት ልዩነት እንዲሆን የመፍትሔ ሃሳብ አቅርቧል።

የማህበሩ ሊቀመንበር ዶ/ር ቻንድ ናግፖል ለቢቢሲ እንደተናገሩት "ክትባቱ በ12 ሳምንታት ልዩነት ቢወሰድ አስተማማኝነቱ ሊቀንስ ይችላል" የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የመንግሥት የኮሮናቫይረስ መግለጫ እንደሚያሳየው በመላው ዩናይትድ ኪንግደም እስካሁን ከ5 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ክትባቱን ወስደዋል።

የእንግሊዝ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ሰኞ ዕለት በመላው እንግሊዝ አዳዲስ የክትባት ጣቢያዎችን ለመክፈት ተዘጋጅቷል።

32ቱ ተጨማሪ ጣቢያዎች ሰኞ ዕለት የጤና እና ማሕበራዊ እንክብካቤ ሞያተኞችን ቅድሚያ ይሰጣሉ። በአንጻሩ ማክሰኞ ደግሞ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሕሙማን እንደሚከተቡ ተገልጿል።

ይህም በብዛት የመከተቢያ ቦታዎቹን በመላው እንግሊዝ ወደ 49 ከፍ ያደርገዋል ተብሏል።

በተጨማሪም 70 ፋርማሲዎች፣ 1 ሺህ ጠቅላላ ሐኪሞች ያሉባቸው ስፍራዎች እና 250 ሆስፒታሎችም ክትባቱን ያቀርባሉ።

የስኮትላንድ ተቀዳሚ ሚንስትር ኒኮላ ስቱርጂን አርብ ዕለት እንደተናገሩት ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆኑት ከ80 በላይ የእድሜ ባለጸጎች የመጀመሪያ ክትባቱን መውሰዳቸውን ገልጸዋል። በሰሜን አየር ላንድም ከ80 ዓመት በላይ የሚሆኑት አረጋዊያን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ተከትበዋል ተብሏል።

በረዶ የበዛበት የአየር ጸባይ በመፈጠሩ በዌልስ አራት የክትባት ጣቢያዎች ተዘግተዋል። ፕሮፌሰር ቫን-ታም ዩናይተድ ኪንግደም ቅድሚያ የሚሰጣቸውን እየተከተቡ ነገር ግን በአዲስ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ አለባቸው ብለዋል።