የትራምፕ ልጆች ሪፐብሊካኖችን ‘አባታችንን አልደገፋችሁም’ ብለው ተቹ

የትራምፕ ልጆች ሪፐብሊካኖችን 'አባታችንን አልደገፋችሁም' ብለው ተቹ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሁለት ልጆች ሪፐብሊካኖች አባታቸው ምርጫውን ለማሸነፍ የሚያደርጉትን ትግል እንዳልደገፉ ተናገሩ።

የትራምፕ ትልቁ ልጅ ዶን ጁንየር [ትንሹ]፤ ፓርቲው “ደካማ ነው” ሲል፤ ኤሪክ ደግሞ “እንደ በግ መንጋ ከሆናችሁ መራጮች መቼም አይረሱትም” ብሏል።

የትራምፕ ልጆች ፓርቲውን ማብጠልጠል የጀመሩት አባታቸው ከፓርቲው ጋር አለመጣጣም መጀመራቸውን ተከትሎ ነው።

ጆ ባይደን ምርጫውን የማሸነፍ እድላቸው እየሰፋ ነው።

ትራምፕ ያለ ማስረጃ ምርጫው ‘ተጭበርብሯል’ ብለው፤ ክስ እንደሚመሰርቱ አስታውቀዋል።

እንደ ሚት ሮምኒ ያሉ ከፍተኛ የሪፐብሊካን መሪዎች በተቃራኒው የትራምን ንግግር ኮንነዋል።

የፖለቲካ ዝንባሌ ያለው ዶን ጁንየር በ2024 ለፕሬዘዳንትነት የሚደረገውን ውድድር ሳይቀር ከወዲሁ ተችቷል።

በትዊተር ገጹ “በ2024 ለፕሬዘዳንታዊ ምርጫ እንቀርባለን ብለው የሚያስቡ መላው የሪፐብሊካን አባላት አንዳች እርምጃ አለመውሰዳቸው ይደንቃል” ብሏል።

ዶን ጁንየር “ለትግል ዝግጁ እንደሆኑ ማሳየት ይችሉ ነበር። ግድ የለም ትራምፕ አሸንፎ ይታገላል። እነሱም እንደተለመደው ዳር ሆነው ይመለከታሉ” ሲልም ተናግሯል።

ማይክ ኮርኖቪች የተባለ የወንዶች መብት ተሟጋችና የትራምፕ ደጋፊ፤ ትዊተር ላይ የቀድሞው የአሜሪካ የተባበሩት መንግሥታት ወኪልን የሚነቅፍ ጽሁፍ ማስፈሩን ተከትሎ ነው የፕሬዘዳንቱ ልጅ የተቆጣው።

የፕሬዘዳንቱ ልጅ፤ ሪፐብሊካኖች ለአሠርታት ደካማ መሆናቸው ግራ ዘመሞች ያሻቸውን እንዲያደርጉ መንገድ ጠርጓል ሲልም ተደምጧል።

ኤሪክ ደግሞ “ሪፐብሊካኖች የት አሉ! ይህን ወንበዴ ታገሉት” ሲል ተናግሯል።

ወንድማማቾቹ ጥሩ ድጋፍ አሳይተዋል ያሏቸውን ሪፐብሊካኖች አሞግሰዋል።

ትራምፕ በአራት ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው ሪፐብሊካኖች ላይ ጫና በማሳደር ያሻቸውን ውሳኔ አሳልፈዋል።

የፓርቲው ማኒፌስቶ ተሰርዞ “የፕሬዘዳንቱን አሜሪካ ትቅደም አጀንዳ መደገፍ” በሚል ቃል ኪዳን ተተክቷል።

የትራምፕና የፓርቲያቸው አለመግባባት ፓርቲው በ2020 ወይም በ2024 ምርጫ ምን አቅጣጫ ይይዛል? የሚለውን አጠያያቂ አድርጎታል።