ኖቤል፡ የዘንድሮ የኖቤል የሰላም አሸናፊ ይፋ ተደረገ

የ2020 የሰላም ኖቤል ተሸላሚ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ፐሮግራም ሆኗል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የ2020 የሰላም ኖቤል ተሸላሚ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ፐሮግራም ሆኗል

በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማት የዘንድሮ አሸናፊ ከጥቂት ደቂቃዎቸ በፊት ይፋ ሆኗል፡፡

የ2020 የሰላም ኖቤል ተሸላሚ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ፐሮግራም ሆኗል፡፡

ድርጅቱ አሸናፊ የሆነው በዓለም ላይ ረሀብ እንደ ግጭትና ጦርነት መሣሪያ እንዳይውል ላደረገው ጥረት ነው፡፡

የኖርዌጂያን የኖቤል ኮሚቴ እንዳለው የዓለም የምግብ ፕሮግራም ድርጅት 10 ሚሊዮን የስዊድሽ ክሮነር ወይም 1.1 ሚሊዮን ዶላር ይሸለማል፡፡

መቶ አንደኛው የሰላም ኖቤል አሸናፊ በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ ነው ይፋ የተደረገው፡፡ ሌሎች የኖቤል ሽልማቶች ባለፉት ቀናት በስቶክሆልም ይፋ መደረጋቸው ይታወሳል፡፡

የዎርልድ ፉድ ፕሮግራም ኃላፊ ይህ የምንኮራበት ቅጽበት ነው ብለዋል፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም እንደሚለው በዓለም ላይ በዚህ ዓመት ብቻ 97 ሚሊዮን ሕዝብ ከረሀብ ታድጓል፡፡ ይህንንም ተግባር የፈጸመው በ88 አገራት ውስጥ ነው።

የዘንድሮውን የኖቤል ሽልማት ካገኙ መካከል በሥነ ጽሑፍ ዘርፍ አሜሪካዊቷ ገጣሚ ሉዊስ ግሉክ ይገኙበታል።

የሄፒታይተስ ሲ ቫይረስን ያገኙት ሦስት ሳይንቲስቶች ደግሞ በሕክምና ዘርፍ ተሸልመዋል። ሳይንቲስቶቹ እንግሊዛዊው ማይክል ሆግተን እና አሜሪካዊያኑ ሀርቪ አልተርና ቻርልስ ራይስ ናቸው።

የዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማት ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከኤርትራ ጋር ሰላም በማምጣታቸው ማሸነፋቸው አይዘነጋም፡፡

እአአ 2009 ላይ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ሽልማቱ ተሰጥቷቸዋል። ኦባማ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የዲፕሎማሲ ግንኙነት በማጠናከር እና ሕዝቦችን በማስተሳሰር ነበር የተሸለሙት።

ከዚህ ቀደም የመብት ተሟጋቿ ማላላ ዮሳፍዚ (በ2014)፣ የአውሮፓ ሕብረት (በ2012)፣ የተባበሩት መንግሥታት እንዲሁም የቀድሞ ጸሐፊው ኮፊ አናን (በ2001) እንዲሁም ማዘር ቴሬሳ (በ1979) ተሸልመዋል።

በስዊድናዊው የፈጠራ ሰው አልፈርድ ኖቤል አማካይነት በ1901 የተጀመነው ኖቤል፤ በተለያየ ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች ወይም ተቋሞች ይሰጣል።

ተሸላሚዎች በልዩ ጥበብ የተሠራ ዲፕሎማ፣ ሜዳልያ እና ገንዘብ ይበረከትላቸዋል።

ሁለቱን የዓለም ጦርነቶች ጨምሮ ሽልማቱ ሳይሰጥ የተዘለለባቸው ወቅቶች ነበሩ።

ከዘርፎቹ በአንዱ ሽልማቱ የሚገባው ሰው ወይም ተቋም ከታጣ ገንዘቡ ወደሚቀጥለው ዓመት ውድድር ይዘዋወራል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ለዓለማችን የላቀ አስተዋፅኦን ላበረከቱ ሰዎች የሚሰጠው የኖቤል ሽልማት አጀማመር።