ኮሮናቫይረስ፡ በአባቱ ቀብር ላይ እናቱን በአካላዊ ርቀት ምክንያት ለማፅናናት ያልቻለው ግለሰብ

በአባቱ ቀብር ላይ እናቱን ለማፅናናት አቅፏት የነበረው እንግሊዛዊ አካላዊ ርቀትህን ጠብቅ መባሉ በከፍተኛ ሁኔታ እንዳበሳጨው ገልጿል።

ክሬይግ ቢክኔል ይህ የተነገረው ክራውንሂል በተባለው የቀብር ስነ ስርአት አስፈፃሚ ሰራተኛ ነው።

ክሬይግም ሆነ ወንድሙ ወንበራቸውን ራቅ አድርገው እንዲቀመጡ ከመንገር በተጨማሪም የኃዘን ስነ ስርአቱም እንዲቋረጥ ተደርጓል።

በኃዘን ልቧ ተሰብራ ከነበረው እናቱ ጎን ተቀምጦም በማፅናናትም ላይ እንደነበረ ተናግሯል።

የሚልተን ኬይንስ ምክር ቤት በበኩሉ በተፈጠረው ሁኔታ ማዘኑንና ለወደፊቱም የተሻለ አማራጭ እንጠቀማለንም በማለት ምላሽ ሰጥቷል።

የ43 አመቱ ክሬይግ በበኩሉ "እናቴን ማፅናናት እንደምፈልግ ለሁሉም ተናግሬ ነበር። በከፍተኛ ሁኔታ ሃዘኗም ጨምሮ ስብርብር ስትል አቀፍኳት" ብሏል።

በአባቱ የኃዘን ስርአት ላይ ወንበሮቹ አካላዊ ርቀትን በሚያስጠብቅ መልኩ ተራርቀው የነበረ ሲሆን የናቱንም የበረታ ኃዘንም ተመልክቶ ወደናቱ የተጠጋ ሲሆን ወንድሙም ተከትሎት እናታቸውን ማፅናናት ጀመሩ።

የቀብር አስፈፃሚ ሰራተኞቹም ወንበሮቹን በየቦታቸው እንዲመልሱና ማንቀሳቀስ አትችሉም ተብለዋል።

በዚህ ሃዘን ላይ እያሉ እንዲህ መባላቸው ከፍተኛ ንዴትና ሃዘን እንደፈጠረበትም ገልጿል።

"በከፍተኛ ሁኔታ የባዶነት ስሜት እንዲሰማኝ አድርጓል" ያለው ክሬይግ የኃዘን ስርአቱ እንዲቀጥልና በሰላም እንዲጠናቀቅም ከራሱ ጋር ትግል ማድረግ ነበረበት።

"ፈታኝ ነበር። የአባቴ የኃዘን ስርአቱ እንዲቀጥልም ውሳኔ ላይ መድረስ ነበረብኝ" ያለው ክሬይግ አክሎም

"በጣም ያዘንኩበትና የፈራሁበትም ወቅት ነው፤ እንዲህ አይነት ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም" ብሏል።

የሚልተን ኬይነስ ምክር ቤት በበኩሉ ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነት ሁኔታ ተፈፅሞ እንደማያውቅና ቤተሰቡንም በማሳዘናቸው ይቅርታ ጠይቀዋል።

የኃዘንም ሆነ የቀብር አስፈፃሚዎች የአንድ ቤተሰብ አባላት ሰብሰብ ብለው ቢቀመጡም ችግር እንደሌለው ትዕዛዝ ተላልፎላቸዋል ብለዋል።

የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በኃዘንም ሆነ በቀብር ስርአት ላይ መገኘት ያለባቸው 30 ሰዎች መሆናቸው በመመሪያው ላይ የተቀመጠ ሲሆን እነሱም አካላዊ ርቀትን በጠበቀ መልኩ መሆኑንም አስፍሯል።