ሞዛምቢክ ፡ መንግሥት አንዲት ሴት ስትገደል የሚያሳየውን ቪዲዮ አጣራለሁ አለ

ከተንቀሳቃስ ምስል ላይ የተወሰደ

የፎቶው ባለመብት, TWITTER/ @ZENAIDAMACHADO

የሞዛምቢክ ባለስልጣናት በነዳጅ ሀብቷ በታወቀችው የካቦ ዴልጋዶ ግዛት ወታደራዊ የደንብ ልብስ የለበሱ ግለሰቦች ራቁቷን ያለች ሴት ደብድበው ሲገድሉ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል መውጣቱን ተከትሎ ምርመራ እንደሚካሂድ ገለፁ።

የመከላከያ ሚኒስትሩ በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ የሚታየውን ድርጊት "ጭካኔ የተሞላበት" በማለት "እውነተኛነቱን እንደሚያጠሩ" ተናግረዋል።

የመብት ተሟጋቾችም ግድያውን አውግዘዋል።

ሞዛምቢክ ላለፉት ሦስት ዓመታት በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ከእስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች ጋር ፍልሚያ ላይ ነች።

የሞዛምቢክ ጦርም ከአማፂያኑ ጋር በሚያደርገው ፍልሚያ በሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚወነጀል ሲሆን፣ መንግሥት ግን የሚቀርብበትን ክስ ያስተባብላል።

ተንቀሳቃሽ ምስሉ የሁለት ደቂቃ ርዝማኔ ያለው ሲሆን በተለያዩ የመብት ተሟጋቾች ሰኞ ዕለት በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ላይ ተጋርቷል።

የወታደሩን ደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች አንዲት ራቁቷን ያለች ሴት ከበው በዱላ ከደበደቧት በኋላ በጥይት ተኩሰው ገድለዋታል።

እንደ ሮይተርስና ኤኤፍፒ ዘገባ ከሆነ ግለሰቦቹ "ግደላት" እያሉ በፖርቹጋል ቋንቋ ሲነጋገሩ እንዲሁም "አልሸባብ ነሽ" ሲሏት ይሰማል።

የሞዛምቢክ መከላከያ ኃይል ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ እንዲህ አይነት ጭካኔ የተሞላበትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የታየበትን ተግባር እንደሚያወግዝ አስታውቋል።

እንደ ሮይተርስ ዘገባ አልሸባብ በአገሪቱ ሰሜናዊ ግዛት ከሦስት ዓመት በፊት ጀምሮ በሰነዘረው ጥቃት 1ሺህ 500 ሰዎች ሲሞቱ 250 ሺህ ያህሉ ደግሞ ተፈናቅለዋል።

ባለፈው ሳምንት አምንስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መግለጫ አረጋገጥኩት ባላቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎች ላይ ወታደራዊ ኃይሉ ከእስላማዊ ታጣቂ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ እስረኞችን ሲያጉላላ፣ እንዲሁም ሲገድል እንደሚታይ ገልጿል።

መንግሥት ግን ውንጀላውን አስተባብሎ፣ ታጣቂዎቹ የወታደሩን ልብስ በመልበስ እንደሚያጭበረብሩ ገልጿል።

ካቦ ሌልጋዶ በአፍሪካ ትልቁ ነው የተባለ የተፈጥሮ ጋዝ የሚገኝባት ስፍራ ነች።

በዚህች ግዛት ኤክሶን ሞቢል 60 ቢሊየን ዶላር በማውጣት የተፈጥሮ ጋዙን ለማልማት እየሰራ ነው።