ኦሮሚያ፡ የታመመ ግመል ስጋ የበሉ ከ100 በላይ ሰዎች መታመማቸው ተሰማ

ግመል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የታመመውን ግመል አርደው ስጋውን ተካፋፍለው የበሉ 110 ጎረቤታሞች ሰዎች መታመማቸው ተነገረ።

ባሳለፍነው ሳምንት የታመመ ግመል ስጋ ተመግበው ሕመም ያጋጠማቸው ሰዎች ቦርቦሪ ተብሎ በሚጠራ ጤና ጣቢያ ሕክምና እንደተደረገላቸው ተጠቁሟል።

የመጨረሻዋ ታማሚም እሁድ እለት በጤና ጣቢያ ውስጥ የሚደረግላትን ሕክምና አጠናቃ ከማዕከሉ መውጣቷ ተነግሯል።

የግመሉን ስጋ ተመግበው ከታመሙ ሰዎች መካከል አንዷ መሆናቸውን የሚናገሩት ወ/ሮ ቦሪ ጃርሶ፤ ስጋውን አብስለው ቢመገቡም ለህመም መዳረጋቸውን ተናግረዋል።

“ባለ ግመሉ ሰውዬ ጎረቤታችን ነው። ግመሉ ሲታመም የተለያየ ባህላዊ መድሃኒት ሲያጠጡት ነበር። ግመሉ ግን ሕመሙ እየተባባሰበት ሲሄድበት ታረደ። ለእኛም ስጋው ተልኮልን ተካፍለን በላን” ይላሉ።

ስጋውን አብስለው የተመገቡ ሰዎች ጨምሮ በሙሉ በሰዓታት ልዩነት ውስጥ መታመማቸውን ወ/ሮ ቦሪ ይናገራሉ።

“ራስ ምታት እና ማስመለስ ያለው ከፍተኛ ህመም ነው ያስከተለብን። ፈጣሪ እና ሐኪም ነው ያዳኑን እንጂ ከፍተኛ ህመም ነበር ያጋጠመን። አሁንም ድረስ የሕመሙ ሰሜት ከውስጣችን አልወጣም” ብለዋል።

በቦርቦር ጤና ጣቢያ ነርስ የሆኑት አቶ ኮከብ መሐዲ በቅድሚያ ወደ 20 የሚጠጉ ሰዎች ታመው መምጣታቸውን ይናገራሉ።

“እንደ ተቅማጥ፣ ማስመለስ እና የሰውነት ሙቀት ያሉ ተመሳሳይ ምልክት ይታይባቸው ነበር” ያሉ ሲሆን፤ ተመሳሳይ የሕመም ምልክት የሚያሳዩ ሰዎች ወደ ጤና ጣቢያቸው በብዛት መምጣት መጀመራቸውን ይናገራሉ።

“በአጠቃላይ 110 ሰዎች አክመናል” ብለዋል።

በአጠቃላይ የታመመውን የግመል ስጋ በልተው የታመሙ ሰዎች በእድሜ ከ1 ዓመት እስከ 70 ድረስ እንደሆኑ ያስታወሱት አቶ ኮከብ ለታመሙ ሰዎች በተሰጠው ህክምና የሰዎች ህይወት እንዳለለፈ ተናግረዋል።

በቦረና ዞን ዳሲ ወረዳ የእንስሳት ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ፍራኦል ዋቆ ማህበረሰቡ የታመሙ እንስሳት ስጋ እና ጥሬ ስጋን መመገብ ማቆም ይኖርበታል ይላሉ።

“የእንስሳት በሽታ በሰው ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። እንስሳት የሚታመሙት የተመረዘ ነገር በልተውም ሊሆን ይችላል ይህ ደገሞ በሰው ጤና ላይ ጉዳት ያስከትላል። እንስሳት መድሃኒት ወስደው ከሆነ ደግሞ ከማረዳችን በፊት መድሃኒቱ ከሰውነታቸው እስኪወጣ መጠበቅ ይኖርብናል” ይላሉ።