ካሽሚር፡ “መቃወም አንችልም፤ ከተቃወምን እንታሰራለን”

አምና ነሐሴ 5 ላይ ሕንድ የካሽሚርን ልዩ አስተዳደር አንስታ፤ ግዛቲቱን ለሁለት ከፍላለች። ጥብቅ የሰዓት እላፊ ገደብ ተጥሏል። በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረዋል። የግንኙነት መስመሮችም ተቋርጠዋል።
ገደቡ ሚያዝያ ላይ በመጠኑ ቢላላም፤ በኮቪድ-19 ምክንያት በድጋሚ ገደብ ተጥሏል። ቁጣና ፍርሀትን ያጫረው በካሽሚር ላይ የተጣለው ገደብ አንድ ዓመት አስቆጥሯል። ይህን ምክንያት በማድረግም 12 የካሽሚር ነዋሪዎችን ቢቢሲ አነጋግሯል።
የጋዜጠኛዋ ሰንዓ ኢርሻድ ሞት
ጋዜጠኛዋ ሰንዓ 26 ዓመቷ ነው። “በኛ ሙያ የግል ሕይወትና ሥራ መለየት አይቻልም” ትላለች።
በሙያው አራት ዓመታት አስቆጥራለች። ባለፉት ዓመታት የእንቅስቃሴ ገደቦች ቢጣሉም የአምናው አስፈሪ እንደነበር ትናገራለች።
“ምን እየተከናወነ እንደነበር ማወቅ አልቻልንም። እርስ በእርሳችን መረጃ የምንለዋወጥበት መንገድ ተቀይሯል። ሰሚ ለማግኘት አዳዲስ መንገዶች መፍጠር ነበረብን” በማለት ያሉበትን ሁኔታ ትገልጻለች።
ለወትሮውም ከጋዜጠኞች ጋር የማይስማሙት የጸጥታ ኃይሎች፤ ካለፈው ዓመት ነሐሴ ጀምሮ የበለጠ ከፍተዋል።
“አሁን ጋዜጠኞች ይታሰራሉ፣ የመረጃ ምንጫቸውን ይፋ እንዲያድጉ ይገደዳሉ። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ማንኛውንም ነገር ከመጻፌ በፊት ቆም ብዬ ማሰብ ይጠበቅብኛል። ሁሌም እፈራለሁ።”
ቤተሰቦቿ ስለ ደኅንነቷ እንደሚጨነቁ ትናገራለች። ስለ ሥራዋ ለቤሰቦቿ ምንም አትገልጽም።
ልጁን ያጣው አልጣፍ ሁሴን
የ55 ዓመቱ አልጣፍ ልጁን ያጣው የነሐሴ አምስቱን የመንግሥት ውሳኔ ተከትሎ ነው።
የአልጣፍ ልጅ ኡሳይብ 17 ዓመቱ ነበር። ከጸጥታ ኃይሎች ለማምለጥ ሲሞክር ወንዝ ውስጥ ዘሎ ነው ሕይወቱን ያጣው። የጸጥታ ኃይሎች ይህን ድርጊታቸውን ክደዋል።
ወጣቱ ከሞተ አንድ ዓመት ቢሞላም፤ የጤና ተቋም ለቤተሰቡ የሞት ማረጋገጫ ሰነድ ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆነም።
አባቱ አልጣፍ “ኳስ ሊጫወት ወጥቶ በሬሳ ሳጥን ተመለሰ። ፖሊሶች በዛን ቀን ማንም አልሞተም ይላሉ። እንደተገደለ ማመን አልፈለጉም። ምስክር ቢኖረኝም ጉዳዩን ለመከታተል ፍቃደኛ አይደሉም። ፖሊስ ጣቢያ፣ ፍርድ ቤት ብንሄድም ፍትሕ አላገኘንም” ይላል።

የስድስት ዓመቷ ሙኒፋ ናዚር
የስድስት ዓመቷ ሙኒፋ በወንጭፍ ቀኝ አይኗን የተመታችው በተቃዋሚዎችና በጸጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ነው።
“ለብዙ ቀናት ሆስፒታል ነበርኩ። አሁን ብዙም ትዝ አይለኝም። ትምህርት ቤት የተማርኩትን ረስቻለሁ። መቶ ከመቶ እደፍን ነበር። አይኔ ከዳነ በኋላ ሐኪም መሆን እፈልጋለሁ። ሐኪሞች ስላዳኑኝ ደስ ይሉኛል” ትላለች ታዳጊዋ።
ፎቶ ጋዜጠኛው አባቷ እንደሚለው የሙኒፋ አይን ዳግመኛ ማየት አይችልም። የትምህርት ቤት ክፍያ ከአቅሙ በላይ ስለሆነም ልጁን አስወጥቷታል።
“የሚታየኝ ጭላንጭል ብቻ ነው። መጻሕፍት ማንበብ አልችልም። የትም አልሄድም። ሐኪሞች ከ15 ቀናት በኋላ ትምህርት ቤት መሄድ ትችያለሽ ቢሉኝም አንድ ዓመት አልፎኛል።”
ባለ አውቶብሱ ፋሩቅ አህመድ
ፋሩቅ 34 ዓመቱ ነው። ታዳጊ ሳለ ካሽሚር ውስጥ ከአውቶብስ ሹፌሮች ጋር ይሠራ ነበር።
2003 ላይ ያጠራቀመው ገንዘብ ላይ የባለቤቱን ወርቅ ሸጦ ገንዘብ ጨምሮበት የራሱ አውቶብስ ገዛ።
አሁን የሰባት አውቶብስ ባለቤት ቢሆንም የትራንስፖርት ዘርፉ እንደቀድሞው እየተንቀሳቀሰ አይደለም።
“400 ሺህ ሩፒ ከፍለን የመኪኖቹን ኢንሹራንስ አሳድሰናል። ግን ምንም ገቢ የለንም። ሰባት ሠራተኞቼ ለረሀብ ተጋልጠዋል። የራሴ ቤተሰብ መከራ ውስጥ ሆኖ እንዴት የነሱን ልረዳ እችላለሁ? እንደኔ አይነት ሰዎች ጥሪታችንን አሟጠን ነው ንግድ የምንጀምረው። ገቢ ከሌለን እንዴት እዳችንን መክፈል እንችላለን?”
ፋሩቅ እዳዎቹን ለመክፈል ሲል የቀን ሥራ ጀምሯል።
የፋሽን ዲዛይነሯ ኢቅራ አህመድ
የ28 ዓመቷ ኢቅራ የራሷን የፋሽን ድርጅት የከፈተችው የማንም ተቀጣሪ ላለመሆን ነው።
በድረገ ገጽ በምትሸጣቸው ሥራዎቿ የካሽሚርን ባህል ማስተዋወቅ እንደምትፈልግ ትናገራለች።
“ኢንተርኔት መዘጋቱ ንግዴን አቀዝቅዞታል። 2ጂ ደግሞ ምንም ጥቅም የለውም። አሜሪካ፣ ዱባይና አውስትራሊያም ደንበኞች አሉኝ” ትላለች።
2ጂ ኢንተርኔት ደካማ ስለሆነ የምትሠራቸውን ልብሶች በድረ ገጽ ማስተዋወቅ አልቻለችም። ቀድሞ በሳምንት ከ100 እስከ 110 የሥራ ትዕዛዝ ታገኝ ነበር። አሁን ግን ቢበዛ ስድስት ልብስ እንድትሠራ ብትታዘዝ ነው።
ዓለም አቀፍ ደንበኞቿ ያዘዙት ልብስ ሳይደርሳቸው ይዘገያል ብለው ይሰጋሉ። በቅርቡ አንድ ልብስ ለመላክ ስድስት ወር ወስዶባታል።
“ንግዴ በዚህ ሁኔታ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ አይመስለኝም። ወርሀዊ ወጪዬ 200 ሺህ ሩፒ ነው። ምንም ገቢ ካላገኘው እንዴት ለሠራተኞቼ ደሞዝ እከፍላለሁ?”

የሕግ ተማሪዋ ባድሩድ ዱጃ
“ሕገ መንግሥቱን፣ ዴሞክራሲ ምን ማለት እንደሆነና ስለ መሠረታዊ መብት አጠናለሁ። እነዚህ ግን ከቃላት ያለፉ አይደሉም። የገነቡት ቤተ መንግሥት እየፈረሰ ነው። ነፃነታችንን እያጣን ነው። ለመምህራንም ይሁን ለተማሪዎች ሕግ መማር ቀልድ ሆኗል” ትላለች የ24 ዓመቷ የሕግ ተማሪ ባድሩድ።
ባድሩድ የመረጠችው ዘርፍ ላይ ጥያቄ ማንሳት ጀምራለች። ጭቆናውንም እንዲህ ትገልጻለች. . .
“መናገር ፈውስ ነበር። አሁን ግን ያሳስራል። ካሽሚር ውስጥ በሚገኝ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ውስጥ ስሠራ ከጋዜጠኞች ጋር በማውራቱ የታሰረ ሰው ገጥሞኛል። ተስፋችን ጨልሟል። ሕግ የተማርነው ሕግ እንዲያስከብሩ የሚከፈላቸው ሰዎች ሕግ ሲጥሱ ለማየት አይለም። ሌላ ሥራ መፈለግ ጀምሬያለሁ።”
ፖለቲከኛው ማንዙር ባህት
ማንዙር 29 ዓመቱ ነው። ሕንድን የሚያስተዳድረው ባህራታያ ጃናታ የተሰኘው ፓርቲ የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊ ነው።
ፓርቲውን በመቀላቀሉ ቤተሰቦቹ እና ጓደኞቹ እንዳገለሉት ይናገራል። እሱ ግን የአካባቢውን ሰዎች እያገዘ እንደሆነ ነው የሚያምነው።
“ህልሜ ስልጣን መያዝ ወይም ሀብት ማካበት ሳይሆን የሰዎችን ሕይወት መለወጥ ነው። ወጣቶች የሚያነሱት መሣሪያ መፍትሔ አይሆንም። በካሽሚር የሚሞቱት ወንድሞቼ ናቸው። ግጭት መልስ አይሆነንም።”
አስጎብኚው ጃቪድ አህመድ
የ35 ዓመቱ ጃቪድ ላለፉት ዓመታት በመርከብ ቱሪስቶችን እያጓጓዘ በቀን ወደ 500 ሩፒ ያገኝ ነበር።
“አሁን ሕይወቴን የምገፋው አትክልት እየሸጥኩ ነው። ግን እንቅስቃሴ ስለተገደበ ገበያ የለም” ይላል።
ጃቪድ ለልጆቹ ትምርት ቤት መክፈል አዳግቶታል። መንግሥት ለእያንዳንዱ መርከበኛ 1000 ሩፒ ለመስጠት ቃል ቢገባም፤ ገንዘቡ የመብራት ክፍያን እንኳ አይሸፍንም።
“ነጋችን ጨምሟል። ቱሪስቶች ስለሚፈሩ አይመጡም። ያለንበት ወቅት ለካሽሚር ነዋሪዎች ከባድ ሆኗል። በተለይ ቱሪዝሙ በጣም ተቀዛቅዟል። ተስፋ ስለቆረጥኩ ለፈጣሪ ትቼዋለሁ።”

ታዳጊዋ ፋላህ ሳላህ
የ12 ዓመቷ ፋላህ “በተቀረው ሕንድ ታዳጊዎች የተሻለ የትምህርት እድል አላቸው። እኔ ግን መሠረታዊ ትምህርት ማግኘት አልቻልኩም። በዚህ እድሜ አስፈላጊውን እውቀት ካላገኘን በፈተና ተወዳዳሪ መሆን አንችልም” ትላለች።
ፋላህ መሠረታዊ የሳይንስ እና ሒሳብ እውቀት እንደሌላት ትናገራለች። ኢንተርኔት በመቋረጡ ምክንያት ለጥያቄዎቿ መልስ ማግኘትም አልቻለችም።
“አሁን ኢንተርኔት ቢመለስም በጣም ዝግ ያለ ነው። መጽሐፍ ላንብብ ብልም የተጻፈውን መገንዘብ አልችልም” የምትለው ፋላህ፤ ትምህርት ቤትና ጓደኞቿ እንደናፈቋት ትናገራለች።
“ለዓመት ከቤት አልወጣሁም። ሌላ አገር ውስጥ ለአንድ ዓመት እንቅስቃሴ ቢቆም ተማሪዎች ተቃውሞ ይወጡ ነበር። እኛ ግን መቃወም አንችልም። ከተቃወምን እንታሰራለን።”
የሆቴል አስተዳዳሪው ሳጂድ ፋሩቅ
ሳጂድ ሆቴል አስተዳዳሪ ነው። አያቶቹና ቤተሰቦቹም ነጋዴ የነበሩት የ43 ዓመቱ ሳጂድ በካሽሚር ተስፋ ቆርጧል።
በ1990ዎቹ የሕንድ አገዛዝን በመቃወም እንቅስቃሴዎች ከተጀመሩ ወዲህ ካሽሚር በግጭት እየተናጠች ሰዎች እየሞቱ መሆኑንም ይናገራል።
“ይህ ሆቴል የተሠራው በሦስት ትውልድ ነው። ግን ከ1990ዎቹ ወዲህ እየተንገዳገድን ነው”
ንግዱ አስተማማኝ እንዳልሆነ ሳጂድ ያስረዳል። ሆቴሉ መብራት ቢጠቀምም ባይጠቀምም 200 ሺህ ሩፒ ይከፍላል።
“ነገሮች ይሻሻላሉ ብዬ አልጠብቅም። ካሽሚር ስታዝን የተቀረው አገር ይደሰታል። የተቀረው አገር ሲደሰት እኛ እናዝናለን። ሁሉም ነገር ፖለቲካ ሆኗል። ሁሉም ነገር ውስጥ ግጭት አለ። ታዲያ በዚህ ሁኔታ እንዴት ይነገዳል?”

አርሶ አደሩቢላል አህመድ
የ35 ዓመቱ አርሶ አደር ቢላል ፍራፍሬ ያመርታል። የአየር ሁኔታ መዛባት ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጨምሮበት አጣብቂኝ ውስጥ ስለገባ መሬቱን ለመሸጥ እያሰበ ነው።
“ሥራ አጥ ከሆንን ዓመት ተቆጠረ። አፕል ከ100 ሺህ እስከ 150 ሺህ ሩፒ ገቢ ያስገባ ነበር። ዘንድሮ ግን 30 ሺህ ሩፒ ብቻ ነው ያገኘሁት። ወንድሜ 1200 ሳጥን አፕል ሰብስቦ ገዢ ስላጣ ምርቱን ጣለው። በዚሁ ከቀጠልኩ መሬቴን እሸጣለሁ።”
ሸክላ ሠሪው መሐመድ ሳዲቅ
መሐመድ 39 ዓመቱ ነው። አስፈላጊውን ግብዓት ማግኘት ስላልቻለ የሸክላ ሥራውን ለማቆም ተገዷል።
መንግሥት በቅርቡ ከሌላ አካባቢ ለሄዱ ነጋዴዎች ፍቃድ ስለሰጠ እንደ መሐመድ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ተወላጆች ከሥራቸው ተፈናቅለዋል።
“መንግሥት አፈር እንዳይቆፈር ወስኗል። የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ነው ይላሉ። ለመሆኑ ፍርድ ቤቶች ይህን ሁሉ ዘመን የት ነበሩ? እንደኔ ያሉ ድሆች ቤተሰቦች ጉዳይ ፍርድ ቤቶችን አያሳስባቸውም? በረሀብ ሊገሉን ነው እንዴ? እንቅስቃሴ ስለተገታ የሠራሁትን መሸጥ አልቻልኩም። አዳዲስ የሸክላ ሥራ መሥራት አቁሜ የቀን ሠራተኛ ሆኛለሁ።”















