የጆርጅ ፍሎይድ ግድያን በተመለከተ ከፖሊሶች የተገኘ ተጨማሪ ማስረጃ ይፋ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, TWITTER/RUTH RICHARDSON
በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ የተከሰሰው የፖሊስ መኮንን ጥቁር አሜሪካዊው አንገት ላይ ቆሞ ሟች በሚያጣጥርበት ወቅት ምንም እንዳይናገር ያስጠነቅቀው እንደነበር ከፍርድ ቤት የወጡ ሰነዶች አመለከቱ።
በፖሊሱ ሙሉ ቁጥጥር ስር የነበረው ጥቁር አሜሪካዊ አንገቱ ላይ የቆመውን ፖሊስ መተንፈስ እንዳልቻለ በመግለጽ የሟች እናቱንና የልጆቹን ስም ይጠራ እንደነበረ በፖሊስ መኮንኑ ላይ ከነበረው ካሜራ የተገኘው የድምጽ ቅጂ አመልክቷል።
የተገኙት መረጃዎች በጠበቆች አማካይነት በግድያው ከተከሰሱት አራት ፖሊሶች በአንዱ ላይ እንደ ማስረጃ ፍርድ ቤት ቀርቦበታል።
በወቅቱ በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ውስጥ እጃቸው አለበት የተባሉት አራት ፖሊሶች ወዲያው ከሥራቸው የተባረሩ ሲሆን ለእስርም ተዳርገዋል።
በተለይ በፍሎይድ አንገት ላይ በጉልበቱ ቆሞ የነበረው ዴሪክ ቾቪን የተባለው የቀድሞ የፖሊስ መኮንን ላይ ሁለተኛ ደረጃ ነፍስ ማጥፋትን ጨምሮ በርካታ ክሶች ቀርበውበታል።
ሌሎቹ ሦስቱ ባልደረቦቹ ቶማስ ሌን፣ አሌክሳንደር ኩንግና ቱ ታዎ የተባሉት የቀድሞ የፖሊስ አባላት ለግድያው በመተባበርና በመሳተፍ ክስ ተመስርቶባቸዋል።
የአንደኛው ተከሳሽ ፖሊስ ቶማስ ሌን ጠበቆች የቀረበበት ክስ ውድቅ እንዲደረግ በጠየቁበት ጊዜ ነው የጆርጅ ፍሎይድን የመጨረሻ ደቂቃዎች ክስተቶችን የሚያሳየው የቪዲዮው ቅጂ የድምጽ ግልባጭ ይፋ የተደረገው።
እስካሁን ድረስ የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ በተመለከተ በአንዲት የዓይን እማኝ ተቀርጾ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰራጨውን ቪዲዮን ነው ሁሉም ሰው የሚያውቀው።
ይህ በፍርድ ቤት ይፋ የተደረገው የቪዲዮ የጽሁፍ ግልባጭ ዝርዝር ነገሮችን በማሳየት በግድያው ወቅት በነበሩት ክስተቶች ዙሪያ ግልጽ መረጃን እንደሚሰጥ ተነግሯል።
በፖሊስ መኮንኖቹ ደረት ላይ በተቀመጡ ካሜራዎች አማካይነት በተቀረጸው በዚህ ቪዲዮ ላይ ሟች ፍሎይድ በሚኒያፖሊስ ጉዳና ላይ በፖሊሶቹ የፊጥኝ በተያዘበት ወቅት ከ20 ጊዜ በላይ መተንፈስ እንዳልቻለ ሲናገር ነበር።
ፍሎይድ ሲጋራ ለመግዛት ሐሰተኛ የ20 ዶላር ኖት ለመክፈል ሞክረሃል በሚል ነበር በፖሊሶቹ የተያዘው።
በካቴና ታስሮ ከፖሊሶቹ መኪና ጎን መሬት ላይ በነበረበት ጊዜ አንደኛው ፖሊስ በጉልበቱ አንገቱላይ በቆመበት ጊዜ ፍሎይድ ለመተንፈስ ይጣጣር ነበር ጨምሮም "ልትገድለኝ ነው" እያለ ሲናገር ተደምጧል።
በዚህ ጊዜም ፖሊሱ በማሾፍ መልክ ለመናገር በቂ አየር ካገኘ ዝም ቢል የሚሻለው መሆኑን በመግለጽ "ምንም አትናገር፤ አትጩህ" ሲያስጠነቅቀው ይሰማል።
ይፋ የተደረገው መረጃ እንደሚጠቁመው ፍሎይድ በፖሊሶቹ ሲያዝ ከመጀመሪያው አንስቶ ተባባሪ የነበረ ሲሆን ፖሊሶቹ ወደ መኪናው በመጡበትም ጊዜ በተደጋጋሚ ይቅርታ ሲጠይቃቸው ነበር።
አሁን የተገኘው ማስረጃ ባለፈው ግንቦት ወር በአሜሪካና በተለያዩ የዓለም አገራት ውስጥ ቁጣን ስለቀሰቀሰው የጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ዙሪያ ያሉትን የመጨረሻ ጊዜያትን በግልጽ ያሳያል ተብሏል።















