ቦትስዋና ውስጥ ከ300 በላይ ዝሆኖች ሞተው ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, Supplied
ባለፉት ሁለት ወራት ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታና ምንነቱ ባልታወቀ ምክንያት ቦትስዋና ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዝሆኖች መሞታቸው ተነገረ።
ከግንቦት ወር ጀምሮ በደቡብ አፍሪካዊቷ አገር ቦትስዋና ኦካቫንጎ በተባለው አካባቢ ከ350 በላይ የሞቱ ዝሆኖች አጽም ባልደረቦቻቸው እንዳገኙ ዶክተር ኔል ማኬን ተናግረዋል።
መንግሥት እንዳለው ለዝሆኖቹ ሞት ምክንያቱ ምን እንደሆነ ማንም አያውቅም፤ ከሞቱት ዝሆኖች ላይ የተወሰደው ናሙና ተመርምሮ ውጤቱን ለማወቅ ሳምንታት ይጠይቃል።
ቦትስዋና በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ የዝሆን ቁጥር እያሽቆለቆለባቸው ካሉ አገራት መካከል አንዷ ናት።
በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው በጎ አድራጎት ድርጅት አባል የሆኑት ዶክተር ማካን ለቢቢሲ እንደተናገሩት በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ የአካባቢ ደህንነት ተቆርቋሪዎች በአውሮፕላን ባደረጉት ቅኝት የተመለከቱትን የዝሆኖች ሞት ለመንግሥት አሳውቀው ነበር።
በመጀመሪያው ለሦስት ሰዓት በተደረገው የቅኝት በረራ 169 የሞቱ ዝሆኖች የታዩ ሲሆን ከአንድ ወር በኋላ በተደረገው ምርመራ በአጠቃላይ የ350 ዝሆኖች አስከሬንና አጽም መገኘቱ ተነግሯል።
ባለሙያው ጨምረውም ይህ ከድርቅ ጋር በማይያያዝ ሁኔታ ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ዝሆኖች ሞተው መገኘት አጋጥሞ አያውቅም።
ባለፈው ግንቦት ወር የቦትስዋና መንግሥት እንዳለው ዝሆኖቹን ከአዳኞች ለመከላከል ሲባል ጥርሳቸው በመነሳቱ ለሞቱት ዝሆኖች ምክንያት አደን ሊሆን አይችልም።
ለዝሆኖቹ ሞት ምክንያት ምናልባት መርዝ ሊሆን ይችላል ቢባል እንኳን ሌሎች እንስሳት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመታየቱ ተገልጿል። ባለፈው ዓመት ተፈጥሯዊ በሆነው አንትራክስ ተመርዘው ቢያንስ 100 የሚሆኑ ዝሆኖች መሞታቸው ይታወሳል።
ነገር ግን አሁን ሞተው ለተገኙት ዝሆኖች ሞት ምክንያቱ በምርመራ እስኪታወቅ ድረስ መርዝ ወይም በሽታ ሊሆን እንደሚችል ከመገመት ውጪ የታወቀ ነገረ የለም።
ከሞቱት ዝሆኖች አወዳደቅና በሄዱበትን መስመር የዳናቸውን ቅርጽ በመከተል ዶክትር ማካን እንደገመቱት ዝሆኖቹን ለሞት የዳረጋቸው በአንዳች ምክንያት አጎላቸው ላይ ባጋጠመ ችግር ነው።
ከውሃ ወይም ከአፈር ጋር ተያይዞ የተቀሰቀሰ ከሆነ ምናልባትም ከሰው ወደ ዝሆኖቹ የተላለፈ በሽታ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል። ዶክተር ማካን አሁን አሁን በእንስሳት ላይ መታየት ጀምሯል የተባለው ኮሮናቫይረስም ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ጨምረውም "ይህ ለተፈጥሮ ጥበቃ ከባድ አደጋ ነው፤ ነገር ግን ክስተቱ የሕዝብ ጤና ቀውስ ሊሆን የሚችልበት እድል አለ" ብለዋል።
የአገሪቱ የዱር እንስሳት እና ፓርኮች ባለስልጣናት ለዝሆኖቹ ሞት ምክንያቱ ምን እንደሆነ ስላላወቁ ናሙናዎችን ልከው በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ የሚመጣውን ውጤት እየተጠባበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።














