ኩባንያዎች ፌስቡክ ላይ አናስተዋውቅም ብለው አድመዋል፤ ሁኔታው ሚዲያውን ይገለው ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ለተቃውሞ ማዕቀብን እንደ አንድ መሳሪያ መጠቀም ወይም ማደም አዋጭ መሆኑን ፌስቡክ የተረዳ ይመስላል።
በጎርጎሳውያኑ 18ኛው ክፍለ ዘመን ባርያ ፈንጋይ ስርዓትን ማስወገድ የሚፈልጉ እንቅስቃሴዎች በባርያ ጉልበት የሚመረቱ ምርቶችን እንግሊዛውያን እንዳይገዙ መቀስቀስ ጀመሩ።
ውጤታማም ነበር። ከዚህም ጋር ተያይዞ 300 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ስኳር መግዛትን አቆሙ፤ ይህም ሁኔታ ባርነትን እንዲያስወግድ ከፍተኛ ጫና እንደፈጠረ የታሪክ መዛግብት ያወሳሉ።
በቅርብም "ስቶፕ ሄት ፎር ፕሮፊት' (ጥላቻን ለትርፍ አንጠቀምበት) የተባለው ዘመቻም በቅርቡም ማዕቀብን እንደ ፖለቲካ መሳሪያነት ያለመ እንቅስቃሴ ነው።
ዘመቻውም ፌስቡክ ዘረኛና ጥላቻ የተሞሉ መልዕክቶችን ወይም ይዘት ያላቸውን ፅሁፎችን በማጥፋት ኃላፊነቱን አልተወጣም በሚልም ወንጅሎታል።
ዘመቻውም ትልልቅ ኩባንያዎችን ማስታወቂያቸውን ከፌስቡክ እንዲሁም ከአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች እንዲያቋርጡ አድርጓቸዋል።
ከነዚህም ኩባንያዎች መካከል ፎርድ፣ አዲዳስና ኤች ፒ የሚጠቀሱ ሲሆን ከነዚህ ኩባንያዎችም ቀድመው ኮካኮላ፣ ዩኒሊቨርና ስታርባክስም ማስታወቂያቸውን በፌስቡክ ማሰራጨታቸውን አቁመዋል።
አክሲዎስ የተባለው ሚዲያ እንደዘገበው ማይክሮሶፍት በፌስቡክና ኢንስታግራም ላይ የሚያሰራጨውን ማስታወቂያ ባለፈው ወር "ያልተገባ ይዘት" በሚል ስጋት ማቋረጡን ቢቢሲ አረጋግጧል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሬዲት፣ ትዊችና ሌሎች ሚዲያዎች እንዲሁ የጥላቻ ንግግርን እንዲቆጣጠሩ ጫና ላይ ናቸው ተብሏል።
ማዕቀቡ ምን ያህል ይጎዳዋል?
ማዕቀቡ ፌስቡክን ይጎዳዋል? በአጭሩ መልሱ ይጎዳዋል ነው። ምክንያቱም ፌስቡክ ዋነኛ ገቢውን የሚያገኘው ከማስታወቂያዎች በመሆኑ ነው።
የአቪቫ ኢንቨስተርስ ሰራተኛ የሆኑት ዴቪድ ከሚንግ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በፌስቡክ ላይ እምነት ማጣት እንዲሁም ሞራላዊ እሴቶች የሉትም ብሎ ማመን "የፌስቡክን ቢዝነስ ሊያወድመው" ይችላል።
ባለፈው አርብ የፌስቡክ ድርሻ ስምንት በመቶ የቀነሰ ሲሆን ይህም ማለት ዋና ስራ አስፈፃሚው ማርክ ዙከርበርግን በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ 6 ቢሊዮን እንዲያጣ አድርጎታል።
ነገር ግን ይህ ሁኔታ ከዚህ በላይ ፌስቡክን ሙሉ በሙሉ ይጎዳዋል ወይም ማህበራዊ ሚዲያውን ይገለዋል ለሚለው ጉዳይ ብዙ የታወቀ ነገር የለም።
ምክንያቱም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የአድማ ዘመቻ ሲመታ የመጀመሪያው አይደለም።
በጎርጎሳውያኑ 2017 ታላላቅ የሚባሉ ኩባንያዎች በዩቲዩብ ላይ ማስታወቂያ ማሰራጨት እንደሚያቆሙ አስታውቀው ነበር። ይህም የሆነው ማስታወቂያዎች ዘረኛና ጥላቻ የተሞላባቸው ቪዲዮዎች በዩቲዩብ መለቀቃቸውን ተከትሎ ነው።
ያ የነበረው ማዕቀብም ሆነ አድማ አሁን ተረስቷል። ዩቲዩብ የማስታወቂያ ፖሊሲውን በተወሰነ መልኩ የቀየረ ሲሆን ከሶስት አመታትም በኋላ ሲታይ ምንም አይነት ተፅእኖ እንዳልደረሰበት ነው።
ምናልባም እንደሚታሰበው ማዕቀቡም ሆነ አድማው ፌስቡክን ላይጎዳው የሚችልበትም ምክንያቶች አሉ።
በመጀመሪያ ደረጃ በርካታዎቹ ኩባንያዎች አድማ የሚመቱት የሚቀጥለውን አንድ ወር ብቻ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ፣ በዋነኝነት ፌስቡክ ገቢውን የሚያገኘው ከትንሽ፣ መካከለኛና ትልልቅ ያሉ በሺዎችና ሺዎች ከሚቆጠሩ ኩባንያዎች ነው።
ሲኤንኤን እንደሚለው ባለፈው አመት ፌስቡክ ላይ ከፍተኛ ገንዘብ አውጥተው ያስተዋወቁ 100 ኩባንያዎች 4.2 ቢሊዮን ዶላር ያፈሰሱ ሲሆን ይህ ግን የኩባንያው ስድስት በመቶ ገቢ ነው።
እስካሁንም ድረስ በቁጥር በርካታ የሆኑት መካከለኛ ገቢ ያላቸው ኩባንያዎች ማዕቀቡንም ሆነ አድማውን አልተቀላቀሉም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዲጂታል ዊስኪ የተባለው የማስታወቂያ ኤጀንሲ የስራ ሂደት ዋና ክፍል ማት ሞሪሰን እንደተናገሩት በርካታ ትንንሽ ኩባንያዎች በፌስቡክ ላይ አናስተዋውቅም ማለት አያዋጣቸውም።
ምክንያቱም ለነዚህ ኩባንያዎች በቴሌቪዥን ከማስተዋወቅ ይልቅ በፌስቡክ ላይ ቢያስተዋውቁ ዋጋው ርካሽ እንዲሁም በርካታ ሰዎችንም ከማግኘታቸው አንፃር ፌስቡክን ይመርጡታል ብለዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በፌስቡክ የሚያደርጉትን ማስታወቂያ እንደማያቆሙም አስረግጠው አስረድተዋል።
ፌስቡክ እንደ ድርጅት የተዋቀረበት መንገድ ለማርክ ዙከርበርግ ከፍተኛ ስልጣንም አሸክሞታል። ሁኔታዎችን ለመለወጥም ሆነ ያለመቀየር ኃይሉ ያለው በአንድ ሰው እጅ ነው።
በፌስቡክ ላይ የአክሲዮን ድርሻ ያላቸው ኩባንያዎች ራሱ በማርክ ዙከር በርግ ላይ ተፅእኖ ማሳረፍ አይችሉም። አንድ ነገር ማከናወን ካልፈለገ፤ አልፈለገም፤ በሱ ፈቃድ ይወሰናል።
እስካሁን ባለው ማርክ ዙከርበርግ የመለወጥ ፈቃድ እንዳለው አሳይቷል። አርብ እለትም የጥላቻ መልእክት ይዘት ያላቸውን ፅሁፎች፣ የጥላቻ ተብሎ የሚለጠፍባቸው ሲሆን ከዚህም በኋላ ሌሎች እርምጃዎችም እንደሚኖር አረጋግጧል።
ነገር ግን እነዚህ ለውጦች ጥላቻን ለትርፍ መጠቀምን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ አይችልም። አንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎችም በራሳቸው አንዳንድ እርምጃዎች የወሰዱ አሉ።
በትናንትናው ዕለት ሬዲት ከፀብ አጫሪነትና ተጠቃሚዎች ላይ የቃላት ጥቃት ማድረስ ጋር በተያያዘ በትራምፕ ስም የተፈጠረ የውይይት መድረክ ሚዲያውን እንዳይጠቀሙ ሙሉ በሙሉ እግድ ተፈፅሞባቸዋል። ይሄ የውይይት መድረክ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ይፋዊ የሆነ ቀጥታ ግንኙነት ባይኖረውም ለሳቸው ድጋፍ የሚሰበስቡ መረጃዎችን ያጋራ ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ ትዊች በበኩሉ በትራምፕ የሚመራውን የምረጡኝ ቅስቀሳ በጊዜያዊነት አግዶታል።
በአማዞን ባለቤትነት ስር ያለው ትዊች ሁለት የትራምፕ የምረጡኝ ቅስቀሳ ቪዲዮዎች የጥላቻ ንግግሮችን መመሪያ ጥሷል በሚል ነው።
አንደኛው ከመመረጣቸው በፊት በጎርጎሳውያኑ 2015 ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሜክሲኮ ደፋሪዎችን እየላከች ነው በማለታቸው ሲሆን፤ ሌላኛው በዚህኛው ወር ፕሬዚዳንቱ በአሜሪካዊቷ ቤት ሰብረው የገቡትን ሰዎች በማሞገሳቸው ነው።
ለብዙዎች ማህበራዊ ሚዲያ ድርጅቶች አመቱ ከባድ ነው።
ፌስቡክ ከዚህ የተለየ እጣፈንታ የለውም። ማዕቀቡና አድማው ከቀጠለና ሌሎች ኩባንያዎችም ከተቀላቀሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች እጣፈንታቸው አጣብቂኝ ውስጥ የሚገባ ይሆናል።
















