ትራምፕ የነጭን የበላይነት የሚሰብክ መልዕክት በትዊተር አጋሩ

አወዛጋቢው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያጋሩት ተንቀሳቃሽ ምሥል የነጭን የበላይነት የሚሰብክ ነው።

አንድ ደጋፊያቸው ድምጹን ጎላ አድርጎ "የነጭ የበላይነት ለዘላለም ይኑር!" የሚል አውድ የሚሰጥ ቃል ሲናገር ይሰማል፤ እርሳቸው ባሰራጩት ቪዲዮ።

መልዕክቱን ሲናገር የነበረው ሰው በፍሎሪዳ የጡረተኞች ሕንጻ ለዶናልድ ትራምፕ ድጋፍ ሲያደርጉ ከነበሩት ሰዎች አንዱ ነው።

ዋይት ፓውር "White power" ነጭ አክራሪዎች የሚያዘወትሩት መፈክር ሲሆን ነጭ ከሌሎች ዘሮች ሁሉ የበለጠ ስለሆነ ነጭ ዘር ሌላውን ዘር መግዛት አለበት የሚል መልዕክትን ያዘለ ነው።

በአንዳንድ የአሜሪካ ግዛቶች ይህ መልዕክት በእጅ ምልክት የሚገለጽ ሲሆን የነጭ የበላይነትን ሰባኪዎችና አክራሪዎች በአንድ እጃቸው ጣቶቻቸው የእንግሊዝኛውን "ደብሊው" (W) ሆሄን እንዲወክል በማድረግ ሌላኛውን ደግሞ የ"ፒ" (P) ሆሄን እንዲይዝ አድርገው የበላይነት ይሰብካሉ።

ይህ ፕሬዝዳንቱ ያጋሩት ተንቀሳቃሽ ምሥል በፍሎሪዳው ሰልፍ ላይ የትራምፕ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች ጸያፍ ስድብ ሲሰዳደቡ የሚያሳይ ነው።

ተንቀሳቃሽ ምስሉን ማጋራታቸውን ተከትሎ ትራምፕ የዘረኝነት መልዕክቶችን በማፋፋም በነጭ አክራሪዎች አካባቢ ዳግም የመመረጥ እድላቸውን ለማስፋት እየሞከሩ ነው የሚል ትችት እየተሰነዘረባቸው ይገኛል።

የትራምፕ ቃል አቀባይ ግን ትራምፕ ባጋሩት ቪዲዮ ውስጥ ይህ የነጭን የበላይነት የሚሰብከውን ድምጽ አልሰሙትም ነበር ብሏል።

ዶናልድ ትራምፕ ይህን ቪዲዮ አሰናስለው በትዊተር ሰሌዳቸው በጻፉት መልዕክት የፍሎሪዳ ዘ ቪሌጅስ ነዋሪዎችን ለድጋፋቸው አመሰግነዋል። ዘ ቪሌጅስ በጡረታ ያሉ የሰሜን ምዕራብ ኦርላንዶ ነዋሪዎች ናቸው። የድጋፍ ሰልፉም የተደረገው እዚያው ነበር።

በዚህ ትራምፕ በኋላ ላይ ከትዊተር ሰሌዳቸው ያስወገዱት ተንቀሳቃሽ ምሥል የነጭ የበላይነትን የሚሰብክ መፈክር እያሰማ የነበረው ሰው በጎልፍ ጨዋታ ላይ በምትዘወተር ጉርድ መኪና ቁጭ ብሎ ይታያል።

ሰውየው ድምጹን ከፍ አድርጎ ከወዲያ ማዶ ለሚሰድቡት ሰዎች የአጸፋ መልስ እየሰጠ ይመስላል።

ከወዲያ የሉ ሰዎች ሰውየውን ዘረኛ እያሉ ሲሰድቡት ይሰማል። ሌሎች ደግሞ ናዚ እያሉ ያወግዙታል። በጎልፍ መኪና ላይ የተቀመጠው ሰው "ነጭ ለዘላለም ይግዛ! የነጭ የበላይነት ይለምልም!" ሲል የመልስ ምት ይሰጣል።

በአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ብቸኛው ጥቁር የሪፐብሊካን የምክር ቤት አባል ቲም ስኮት ከሲኤንኤን ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ትራምፕ ያጋሩት ተንቀሳቃሽ ምሥል "ጸያፍ ነው" ካሉ በኋላ ዶናልድ ትራምፕ ምሥሉን ከትዊተር ሰሌዳቸው በአስቸኳይ እንዲያነሱት ጠይቀዋል።

ዶናልድ ትራምፕ አወዛጋቢና የዘረኝነት መንፈስ ያላቸውን መልዕክቶችን በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ ሲያጋሩ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።

በ2017 በተመሳሳይ የእንግሊዝ ቀኝ አክራሪዎችን መልዕክት በማጋራታቸው ከዚያን ጊዜዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ ጋር ቅራኔ ውስጥ ከቷቸው እንደነበር ይታወሳል።

በ2019 ደግሞ የምክር ቤት ተመራጭ የሆኑትን አራት ሴቶች ማለትም ኢልሃን ኦማር፣ አሌክሳድሪያ ኦካሲዮ፣ ራሺዳ ጣላይብ እና አያና ብሬስሊን "ወደመጣችሁበት ሂዱና በወንጀል የተበከለውን አገራችሁን ችግር ፍቱ. . ." በሚል አሜሪካዊ እንዳልሆኑና መጤ እንደሆኑ የሚያሳስብ መልዕክት ጽፈውባቸው ነበር።

ትራምፕ እንዲህ በስድብ የሞለጯቸው ሴት የምክር ቤት አባላት ከአራቱ ሦስቱ እዚያው አሜሪካ የተወለዱ ሲሆን አራቱም የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ናቸው።

ከዚህም ሌላ በቅርቡ የጆርጅ ፍሎይድን በነጭ ፖሊስ በግፍ መገደል ተከትሎ የተነሳውን ተቃውሞ ለማብረድ ፖሊስ የኃይል እርምጃ እንደሚወስድ ትራምፕ የገለጹበት መንገድ ዘረኛ በመሆኑ ሲተቹበት ነበር።

ዶናልድ ትራምፕ "ዘረፋ ሲጀመር ተኩሱም ይጀምራል" የሚለው አገላለጽን መጠቀማቸው ያስተቻቸው፤ ገለጻው በ1960ዎቹ መጨረሻ የማያሚ የፖሊስ ሹም ዋልተር ሄድሌይ ፖሊስ ጥቁሮችን እየለቀመ እንዲገድል መልዕክት ያስተላለፈበት በመሆኑ ነበር።

ዶናልድ ትራምፕ ከእነዚህ ዘረኝነትን ከሚያባብሱ መልዕክቶች ሌላ የኮሮናቫይረስን "ኩንጉ ፍሉ" እያሉ መጥራታቸው ሲያስተቻቸው ቆይቷል።

ይህ አገላለጻቸው በአሜሪካ የሚኖሩ የእስያ መልክ ያላቸው ዜጎች በሌሎች ጥቃት እንዲደርስባቸው እና እንዲገለሉ የሚያደርግ ነው።

የዋይት ሐውስ አዲሷ ቃል አቀባይ ኬይሊ ማክኔኒ ግን ይህን አስተባብላለች።

"ፕሬዝዳንቱ ኩንግ ፍሉ እያሉ ቫይረሱን የሚጠሩት ቫይረሱ ከቻይና ስለመጣ ብቻ ነው" ትላለች።